Friday, July 19, 2013

IV.          ጸሎትና መንፈሳዊ ውጊያ
ስለ መንፈሳዊ ውጊያ ስናስብ ውጊያችን በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ድል ከተመታ ጠላት ጋር መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ ስለ ጌታ ኢየሱስ ድል መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎድል በመንሳት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው›› (ቆላ 2፤15)፡፡ ‹‹እርሱም (ክርስቶስ) መላእክት፣ ሥልጣናት፣ ኃይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ›› (1ኛ ጴጥ 3፤22)፡፡ሰይጣንን በተመለከተ በክርስቲያኖች ዘንድ ሁለት ዓይነት የተሳሳተ ጽንፈኛ (Extreme)አስተሳሰብ ሲንጸባረቅ ይስተዋላል::
አንደኛው ክፍል ሰይጣንን ሁሉን ቻይ እንደሆነና በአንድ ጊዜ በሁሉም ሥፍራ እንደሚገኝ ዓይነት አድርጎ የሚያስብ ይመስላል::እንደዚህ ዓይነት ሰዎች የጌታን ችሎታ ለሰይጣን ይሰጡታል::ሁሌ የሚያስቡት ስለ ሰይጣን ነው::አብዝተው ሰይጣን ስለሰራው ሥራ ይናገራሉ::ሰይጣን ራሱ ስለ ራሱ ብቻ እንድናስብ ይፈልጋል::የጌታን ታላቅነትና የማዳኑን ሥራ ለማወጅ እንጂ የሰይጣንን ዝና ልናወራ አልተጠራንም::ሰይጣን ኅይል ቢኖረውም ውስን ፍጡር ነው::በአንድ ጊዜ በሁሉም ሥፍራ አይገኝም::ከዚህም የተነሣ ለተለያየ የክፋት ተልዕኮው ከሥፍራ ሥፍራ መንቀሳቀስ ግድ ይለዋል(ኢዮብ 1:7)::ለዓመጽ ሥራው ክፉ መናፍስትን በተለያየ ሥፍራ ያሰማራል(ኤፌሶን 6:12)::ሰይጣን በአንድ የጌታ መልአክ ተይዞ የሚታሰር መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ይነግረናል፡- ‹‹የጥልቁንም መክፈቻና ታላቁን ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ የቀደመውንም እባብ ዘንዶውን እርሱም ዲያብሎስና ሰይጣን የተባለውን ያዘው፤ ሺህ ዓመትም አስረው፤ ወደ ጥልቅም ጣለው፤አሕዛብንም ወደ ፊት እንዳያስት ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በእርሱ ላይ ዘግቶ ማኅተም አደረገበት››  (ራእይ  20፡1-3)፡፡ጌታ አእላፋት ጊዜ አእላፋት መላእክት እንዳሉት ቃሉ ያስተምረናል(ራእይ 5:11)::ሆኖም ግን አንድ የጌታ መልአክ ሰይጣንን እንደሚያስረው ከላይ የተጠቀሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ይነግረናል::በመሆኑም ሰይጣንን ከጌታ ጋር በኃይል እንደሚስተካከል አድርገን ልናስብ አይገባም፡፡
ሁለተኛው ዓይነት ጽንፈኛ አስተሳሰብ ደግሞ ለሰይጣን ምንም ግምት ያለመስጠት ነው::ለእንደዚህ ዓይነት ክርስቲያኖች ሰይጣን ያለም አይመስልም::እንደዚህ ዓይነት ክርስቲያኖች አንዴም ሰይጣንን ሲቃወሙት አይስተዋልም::መጽሐፍ ቅዱስ ግን የሰይጣንን መኖር አስረግጦ በመናገር እንድንቃወመው ያዘናል ( ኤፌሶን 6: 10-18)::
ስለ ሰይጣን ሚዛናዊ አስተሳሰብ ሊኖረን ይገባል::የሌለውን ችሎታ ልንቸረው አይገባም::አሠራሩንም ባለማወቅ ጭራሽ የለም ማለትም ለሰይጣን የስህተት አሠራር መጋለጥን ያመጣል:: "በሰይጣን እንዳንታለል የእርሱን አሳብ አንስተውምና"( 2ኛ ቆሮ 2:11)::
የመጀመሪያው ጽንፈኛ አስተሳሰብ የሚንጸባረቀው በአብዛኛው በፔንቴኮስታሉና በካሪዝማቲኩ ክልል ሲሆን ሁለተኛው ጽንፈኛ አስተሳሰብ ደግሞ በአብዛኛው በኢቫንጀሊካል አካባቢ የሚታይ ነው::
ሰይጣን የእግዚአብሔርና የጌታ ልጆች የሆነው የእኛም ጠላት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ አስረግጦ ይናገራል (1ኛ ጴጥ 5: 8-9)::በዚህ አጭር ጽሑፍ ሰይጣንን እንዴት መዋጋት እንደሚገባን ለማሳየት ተሞክሯል::በመጀመሪያ ግን ሰይጣን በክርስቲያን ላይ ሥልጣን አለውን? ሥልጣን ከሌለው ታዲያ እንዴት ነው ኅይሉን ለማሳረፍ መንገድ የሚያገኘው የሚለውን መመልከቱ ይጠቅማል::
ሰይጣን በክርስቲያን ላይ ሥልጣን አለው?
የእግዚአብሔር ቃል እንደሚያስተምረን ሰይጣን በክርስቲያን ላይ አንዳች ሥልጣን (ህጋዊ መብት) የለውም፤ በመሆኑም ኃይሉን እንዳሻው በእኛ ላይ የማሳረፍ መብት የለውም፡፡ "እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን"ይላል (ቆላስይስ 1:13-14)::እግዚአብሔር አንድያ ልጁን በመስቀል ላይ እንዲሞት አሳልፎ በመስጠት የኃጢአት ዕዳችን እንዲከፈል በማድረግ ከጨለማው ሥልጣን አስመልጦን ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፍልሶናል:: በክርስቶስ ሥራ በማመናችን የእግዚአብሔር ልጆች የመሆን ሥልጣን ተሰጠን (ዮሐ.1:12):: ሰይጣን በኛ ላይ ሥልጣን ሊኖረው ይቅርና እንደሁም እኛ ክርስቲያኖች በሰይጣን ላይ ሥልጣን እንዳለን የሚከተለው ክፍል ያስረግጣል፥"እነሆ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥የሚጎዳችሁም ምንም የለም"(ሉቃስ 10:19)::
ሰይጣን በክርስቲያን ላይ ሥልጣን ከሌለው ታዲያ እንዴት ነው ሊያጠቃን የሚችለው? ወይም እንዴት ነው ብዙ ክርስቲያኖች በሰይጣን ጥቃት ውስጥ ሲወድቁ የሚስተዋለው? የሚለው ጥያቄ ሊነሳ ይችላል::ክርስቲያኖች በጠላት ጥቃት ውስጥ የሚወድቁት ሽንገላውን ተቀብለው ለሰይጣን በር ሲከፍቱለት ወይም ሥፍራ ሲሰጡት ነው:: በመሆኑም ቃሉ ‹‹የዲያቢሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ›› (ኤፌሶን 6፤11) ይላል፡፡ አዳምና ሔዋን በሰይጣን ሽንገላ ተታለው በመውደቃቸው የጠላት ፈቃድ ተፈጸመባቸው (ዘፍጥረት 3:1-7ኤፌሶን 2::1-2)፡፡ ሰይጣን የሚያጠቃን በሽንገላው በመታለል በር ስንከፍትለት ነው::ሰይጣንን በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚጠቀሱትን አሳቦች ማጤኑ ስለሰይጣን አሰራር ለመረዳት ጠቃሚ ነው::
"የዲያቢሎስን ሽንገላ" (ኤፌሶን 6:11)
"አሕዛብንም ወደ ፊት እንዳያስት"(ራእይ 20:3)
"በሰይጣን እንዳንታለል"(2ኛ ቆሮ.2:11)
"ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና"(2 ቆሮ11:14)::
"ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራልሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና" (ዮሐ. 8:44)::
"በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት" (2ኛ ቆሮ.11:3)
ሽንገላ፥እንዳያስት፥እንዳንታልል፥እንዲመስልይለውጣል፥ሐሰት፥ሐሰተኛና በተንኮሉ እንዳሳታት የሚሉት ቃላት ስለሰይጣን ማንነትና አሠራር ገላጭ መሆናቸውን መገንዘብ ይኖርብናል::ስለዚህ ዋናው የአሠራሩ ባህሪ ማሳትማስመሰልማታለልናመሸንገል መሆኑን ልናስተውል ይገባል::
በአንጻሩ ደግሞ የጌታ ኢየሱስ ኃይል በሕይወታችን የሚሠራው እውነትን ስንቀበል ነው፡- ‹‹እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም አርነት ያወጣችኋል›› (ዮሐንስ 8፤32)፡፡ የእውነት እውቀት የነጻነት ሕይወት እንድንለማመድ ይረዳል::የእግዚአብሔርን ቃል እውነት ተቀብለን በሕይወታችን ስንተገብረው ነጻነታችን እየጨመረ ይሄዳል፤የሰይጣንን ውሸት ስንቀበል ግን የጭቆና ኃይሉ በላያችን ያርፋል፡፡ በመሆኑም ጌታ ከሰይጣን ውሸትና ሽንገላ የምንጠበቅበትን ማስተዋልና ጥበብ እንዲሰጠን ልንጸልይ ይገባል፡፡ ቃሉ ‹‹በሰይጣን እንዳንታለል የእርሱን ሃሳብ አንስተውም›› (2ኛ ቆሮንቶስ 2:11) ይላል፡፡ በሰይጣን እንዳንታለል የሚረዳን የጌታ ሃሳብ የሆነውን የጌታን ቃል መታዘዝ ነው፡:(1ኛ ቆሮ 2:16)፡፡ ‹‹እባብ (ሰይጣን) በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት…›› (2ኛ ቆሮ 11:3) እንደሚል ቃሉ ለሰይጣን ስህተት አሠራር አልፈን እንዳንሰጥ ከጌታ ዘንድ ሁል ጊዜ ጥበብን ልንጠይቅ ይገባል፡፡
አእምሯችንን ወይም አስተሳሰባችንን ሰይጣን ምሽጉ አድርጎ እንዳይቆጣጠረው ከፍተኛ ጥንቃቄና ውጊያ ልናደርግ ይገባል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ‹‹በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፤ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ የሰውንም ሃሳብበእግዚአብሔር እውቀት ላይ የሚነሳውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን፤ ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን›› (2ቆሮ10፤4-5) ይላል፡፡
ከፍተኛ ውጊያ የሚካሄድበት የሕይወታችን ክፍል አእምሯችን ነው:: አሳባችንን ለመቆጣጠር በጨለማው ኅይል ከፍተኛ ትግል ይካሄዳል፡፡ አእምሯችንን እንደ ምሽጉ አድርጎ ለመቆጣጠር ጠላት የማያነሳው ድንጋይ የማይቆፍረው ጉድጓድ የለም፡፡ በመሆኑም አሳባችንን በእግዚአብሔር ቃል በመሙላት የታደሰ አእምሮ ሊኖረን ግድ ይላል፡፡ በታደሰ አእምሮ ውስጥ ሰይጣን ምንም ስፍራ አያገኝም፡፡ በአሮጌው አስተሳሰብ የሚመራ ወይም በቃሉ ያልታደሰ አእምሮ ያለው ክርስቲያን የጠላትን ሃሳብ ያስተናግዳል፡፡ ከጠላት የሆኑና ለሰይጣን የሚመቹ ሀሳቦችን ሁሉ ማርከን ለክርስቶስ ማስገዛት አለብን፡፡ በእግዚአብሔር እውቀት ላይ የሚነሳ ሃሳብ ወደ አእምሯችን ብቅ ሲል ለክርስቶስ እንዲገዛ ልንማርከው ይገባል፡፡ ያ ሲሆን ሰይጣን በሕይወታችን ለመሥራት ዕድል ያጣል፤ሰላማችንነጻነታችንና በረከታችን ይጨምራል፡፡
አእምሯችንን በተመለከተ ሰይጣን ሁለት ነገር ማድረግ እንደሚችል ከመጽሐፍ ቅዱስ እንረዳለን፡-
1ኛ) አሳቡን ወደ አእምሯችን ማስገባት ይችላል፡- ‹‹ዲያብሎስ በስምኦን ልጅ በአስቆርቱ ይሁዳ ልብ (አእምሮ) አሳልፎ እንዲሰጠው አሳብ ካገባ በኋላ…›› (ዮሐንስ 13፤2) ይላል ቃሉ፡፡ በመሆኑም ወደ አአምሯችን የሚላኩ ሃሳቦችን ሁሉ ልንመረምር ይገባል፡፡ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የማይስማሙ ከሆነ ወዲውኑ ልንጥላቸው ይገባል፡፡ ጠላት የራሱን ክፉ አሳቦች ወደ አአምሯችን ብልጭ ካደረገ በኋላ ከእግዚአብሔር ነው ብለን እንድንቀበል ይሸነግለናል፡፡ አንዳንድ የዋህ ቅዱሳን በጸሎት ላይ ሳሉ የመጣ ሃሳብ ሁሉ ከጌታ ነው ብለው ያስባሉ፡፡ ይህ ግን ስህተት ነው፡፡ ለጸሎት ተንበርክከንም እንኳ ሰይጣን ሀሳቡን ወደ አእምሯችን ሊልክ ይችላል፡፡ ስለዚህ ሃሳቡ በየትኛውም ሰዓት፣ በማናቸውም ቦታ ይምጣ በሚገባ ልንፈትሸው ይገባል፡፡
2ኛ. ሰይጣን በውስጣችን እንዲቆይ የማይፈልገውን ሃሳብ ከአአምሯችን ውስጥ ይሰርቃል፡፡
የምንባረክባቸውን ሃሳቦችመልካም ራእዮችና የሚያጽናኑ ነገሮችን ከአእምሯችን በመንጠቅ በምትኩ የሚያስጨንቁንንና የሚያረክሱንን ሃሳቦች ወደ አእምሯችን ይልካል፡፡ በሉቃስ 8፡12 ላይ ‹‹ዲያብሎስ ይመጣል፤ አምነውም እንዳይድኑ ቃሉን ከልባቸው (ከአእምሯቸው) ይወስዳል›› ይላል፡፡ብዙ ቅዱሳን አእምሯቸው በሰይጣን የተጠቃ ነው::በተሰበሰበ አእምሮ አንድ ገጽ ጹሁፍ እንኳ ማንበብ አይችሉም::የማይፈልጓቸው እልፍ አሳቦች ወደ አእምሯቸው ይጎርፋሉ::ቃሉን ሲሰሙ የተለያዩ አሳቦች እየመጡ የሚሰሙት ቃል እንዲያመልጣቸው ያደርጋሉ:: የዚህ ሁሉ አሳብ ምንጩ ከየት ነው?ከዲያቢሎስ መሆኑ ምንም ጥርጥር ሊገባን አይገባም::አእምሯችንን እኛ ነን ወይስ ሌላ ኅይል የሚቆጣጠረው?ያስብላል
የቀደመው እባብ (ሰይጣን)፣ ሔዋንን በኤደን ገነት ያሳተው የውሸት ሃሳብ በመስጠት ነበር፡፡ ‹‹አትሞቱም …እንደ እግዚአብሔር ትሆናላችሁ›› የሚል ሃሳብ ለሔዋን አቀረበላት፡፡ ሔዋን የሳተችውሁሉ በሞላበት በኤደን ገነት ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ግን በምድረ በዳ በራበው ወቅት እንኳ ከሰይጣን የቀረበለትን ድንጋይ ወደ ዳቦ የመቀየር ሃሳብ በእግዚአብሔር ቃል በመዋጋት አሸነፈ፡፡ በተጨማሪም እራሱን ከመቅደስ ጫፍ ላይ እንዲወረውር ለሰይጣንም እንዲሰግድ አሳብ ቀርቦለት ነበር፡፡ ለሰይጣን እንዲሰግድ የቀረበለት ሃሳብ ከጉርሻ ጋር ነበር፡፡ ሁሉንም ግን በቃሉ ሰይፍ በመዋጋት አሸነፈ፡፡
ሰይጣንን እንዴት እንቃወመው?
የእግዚአብሔር ቃል ‹‹ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሻሻል›› (ያዕቆብ 4፤7-8) ይላል፡፡ ዲያብሎስን ለመቃወም ምን ዓይነት ስልት ብንከተል መልካም ነው?ከዚህ በታች ሰይጣንን ለመቃወም ወይም ለመዋጋት የሚረዱ ሰባት ስልቶች ተዘርዝረው ተብራርተዋል(ከ ሀ-ሰ):: 
ሀ. ለሰይጣን ዕድል ፈንታ (መቆሚያ) መከልከል
የእግዚአብሔር ቃል ‹‹ለዲያብሎስ ዕድል ፈንታ /መቆሚያ አትስጡት›› (ኤፌን 4፤27) ይላል፡፡ ለዲያብሎስ እድል ፈንታ የሚሰጡትን ነገሮች ከሕይወታችን በማስወገድ ዲያብሎስ የሚሰራበትን መንገድ በማሳጣት ልንቃወም ይገባል፡፡ይህ ሲሆን ሰይጣን ወደ ሕይወታችን የሚገባበትን በር ሁሉ መዝጋት ያስችለናል::
ለሰይጣን መቆሚያ የሚሆኑ ነገሮች ወይም መግቢያ በሮች ምን ምን ናቸው? ዘጠኙን ከዚህ በታች እንመለከታለን፡፡
1.               ተናዝዘን ያልተውነው ኃጢአት
በግልጽም ሆነ በስውር የምንለማመደውና ተናዝዘን ያልተውነው ኃጢአት ለሰይጣን መቆሚያ ይሆናል፡፡ እንዲህ ያለው ኃጢአት ለሰይጣን በር በመክፈት ሰይጣን በሕይወታችን ላይ ጎጂ ተጽእኖ እንዲያመጣ ዕድል ይሰጠዋል፡፡ በሽታን፣የሕይወት ድርቀትንና ሌሎች አሉታዊ ነገሮችን ወደ ሕይወታችን እንዲልክ በር ይከፍትለታል፤ በመሆኑም በእግዚአብሔር ኃይል ተረድተን፣ ከማናቸውም ኃጢአት በመላቀቅ ለሰይጣን ዕድል ልንነፍገው ይገባል፡፡ኃጢአት ከሠራንም ወዲያው በመናዘዝና ንስሐ በመግባት የበደላችንን ስርየት ከጌታ ማግኝት አለብን (1ኛ ዮሐ 1:9)::መናዘዝ ማለት የሠራነውን በደል ለጌታ መንገር ማለት ሲሆን ንስሐ መግባት ማለት ደግሞ ከኃጢአት መንገዳችን መመለስና የጽድቅ ሕይወት መኖር ማለት ነው:: የምንወደው ኃጢአት ካለም በግልጽ ጌታ ከሕይወታችን እንዲነቅልልን ልንማጸነው ይገባል፡፡ ያን ኃጢአት የምንጠላበትንና የምንከዳበትን ጸጋ ጌታ ይሰጠናል፡፡ በክርስቶስ በኩል የተገለጸው ጸጋ ይህን እንድናደርግ ያስችለናል፡- ‹‹ይህም ጸጋ ኃጢአተኛነትንና ዓለማዊ ምኞትን ክደን የተባረከውን ተስፋችንን፣ እርሱም የታላቁን የአምላካችንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ፣ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል›› (ቲቶ 2፡12-13)፡፡
ከጌታ ጸጋ የተነሳ ከተሸናፊነት ወጥተን የድል ሕይወት መለማመድ እንችላለን፡፡ አንዳንድ ክርስቲያኖች በዓለም ሳሉ የተለማመዱት ኃጢአት ለምሳሌ ሴጋ (ማስተርቤሽን)፣ ግብረ ሰዶማዊነት፣ ዝሙት፣ ሲጋራ ማጨስ፣ሐሺሽ መውሰድመጠጥ መጠጣትና የመሳሰሉት ክፉ ልምዶች በጌታ ቤት ውስጥ ሲኖሩም የድል ሕይወት እንዳይለማመዱ ሳንካ ሲሆኑባቸው ይስተዋላል፡፡ ሆኖም ግን በጾምና በጸሎት፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይልና በቅዱሳን የምልጃ ጸሎት እንዲህ ዓይነት ሰዎች ፈጽመው ነጻ ሊወጡ ይችላሉ፡፡ እስራኤልን ከፈርዖን ቀንበር ያላቀቀ ጌታኃጢአተኞችንም ከኃጢአት ቀንበር በትንሳኤው ኃይል ዛሬም ይፈታል፡፡ ብዙዎቻችን ለጌታ ነጻ አውጪ ኃይል ምስክሮች ነን፤ ከብዙ የኃጢአት እስራት ፈቶ ለክብሩ ምስጋና አቁሞናል፡፡እግዚአብሔር ይመስገን::
ፈርዖን እስራኤላውያን የግብፅን ምድር ለቅቀው ሲወጡ ያለ የሌለ ኃይሉን አስተባብሮ ወደ ባርነት ሕይወታቸው ሊመልሳቸው እንደዘመተ፣ ቅዱሳን የሰይጣንን የኃጢአት ቀንበር ወዲያ አሽቀንጥረው በመጣል የቅድስና ኑሮ መኖር ሲጀምሩ ሰይጣን ባለ በሌለ ኃይሉ በመዝመት ወደ ተላቀቁት ኃጢአት ሊመልሳቸው መጣሩ አይቀርም፡፡ ሆኖም ግን ጸንተው ሲቃወሙት እንደ ቃሉ ከእነርሱ ይሻሻል፡፡ እነርሱም በጌታቸው ኃይል ተደግፈው የጽድቅ ኑሮ መኖር ይጀምራሉ፡፡ ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን! ደም እስከማፍሰስ ድረስ ከኃጢአት ጋር ገና አልተጋደልንም፤ አልተቃወምንም (ዕብራውያን 12፡ 4)፡፡ ስለዚህ ኃጢአትን ለመተው የጨከነ ልብ ሊኖረን ይገባል፤ ይህ ሲሆን ጠላት መቆሚያ ስለሚያጣ እሱን ለመቃወም ትክክለኛ ቦታችንን እንይዛለን፡፡
2.           ማናቸውም ጥንቆላ ነክ ነገሮች (ዕቃዎችን) ወደ ቤት ማስገባት
የእግዚአብሔር ቃል ‹‹እንደ እርሱ ርጉም እንዳትሆን ርጉምን ነገር ወደ ቤትህ አታግባ፤ ተጸየፈው፣ ጥላው›› (ዘዳግም 7፡26) ይላል፡፡ እንደ ጨሌ፣ የኮከብ ቆጣሪ ጋዜጣ፣ የክህደት መጻሕፍት፣ የአምልኮተ ሰይጣን መጻሕፍት፣ወሲብ ቀስቃሽ ፊልሞች፣ምስሎች፣ ጽሑፎች (ፖርኖግራፊ)፣ ወዘተ ፈቅደን ወደ ቤታችን ማስገባትና መጠቀም ለሰይጣን ጥቃት ራሳችንን እንድናጋልጥ ያደርገናል፡፡ ወሲብ ቀስቃሽ ምስሎችንና ፊልሞችን የሚመለከት ክርስቲያን የዝሙትና የሴሰኝነት መንፈስ ቢዋጋው ምንም አይገርምም፡፡ እንደነዚህ ያሉ ዕቃዎችን አውጥተን መጣል ወይም ማቃጠል ይገባል፡፡"ከአስማተኞችም ብዙዎቹ መጽሐፋቸውን ሰብስበው በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉት" (ሐዋ ሥራ 19:19):: ቤታችን ከማናቸውም የጠላት መጠቀሚያ ከሆነ ነገር የጸዳ ሊሆን ይገባል::
3.                 ይቅር የማይል ልብ
ይቅር የማይል ልብ ሰይጣን ወደ ሕይወታችን እንዲገባ በር ከፋች ነው፡፡ ሰዎች በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ምክንያቶች ይበድሉን ይሆናል፡፡ ቁርሾ ወይም ቂም መያዝ ለሰይጣን አሠራር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ቆሻሻ ቦታ ዝንቦችን እንደሚስብ ሁሉ ጥላቻ የተሞላ ልብም አጋንንትንና ክፉ ተጽእኖአቸውን ይስባል፡፡ በአንጻሩ ፍቅር የተሞላ ልብ ለሰይጣን አሠራር ምቹ አይደለም፡፡ ለዚህ ነው መጽሐፍ ቅዱስ በተለይም አዲስ ኪዳን ስለ ፍቅር አብዝቶ የሚያስተምረው፡፡
የበደሉንን ሁሉ ይቅር በማለት ለጠላት ዕድል ፈንታ ልንነፍገው ይገባል፡፡ የበደሉንን ሰዎች እየባረክን እንጸልይላቸው፡፡ ያን ጊዜ ልባችን ከጥላቻ ስሜት ይፈወሳል፡- የምንጸልይለትን ሰው መጥላት አንችልምና፡፡ ምክንያቱም ጸሎት ወይም ምልጃ የፍቅር ቋንቋ ነው፡፡ ጠላት የበደሉንን ሰዎች እያስታወሰ ሊያውከን ሲፈልግ ወዲያውኑ ስለ እነዚያ ሰዎች መማለድ እንጀምር፡፡  ጌታ እንዲባርካቸው እንጸልይ፡፡ የሰይጣን አሳብ ይከሽፋል፤ ምክንያቱም ሰይጣን ለማንም እንዲጸለይ ስለማይፈልግ ነው፡፡ስለበደሉን ሰዎች ከልብ በምንጸልይበት ጊዜ ጌታ እኛንም የምንጸልይላቸውንም ሰዎች እንደሚባርክ ሰይጣን ያውቃል፡፡
ስለዚህ እግዚአብሔር ፍቅር እንዲሞላን ልንጸልይ ይገባል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ለሰቀሉት ሰዎች ‹‹የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው›› በማለት የጸለየው ስለሚወዳቸው ነው፡፡ ‹‹ጌታ ሆይ የበደሉኝን ሁሉ ይቅር እንድላቸው በፍቅርህ ሙላኝ›› ብለን ልንጸልይ ይገባል፡፡ ጌታ ጸሎታችንን ሰምቶ በፍቅሩ ይሞላናል፡፡ ሰዎች ሲበድሉን ለመበቀል አንሂድ፡፡ ይቅር አለማለት በቀልን መሞላት ነው፡፡ በዘዳግም 32፡35 ላይ ጌታ በቀልና ፍርድ የእርሱ እንደሆኑ ተናግሯል፡፡ ስለዚህ ሰዎችን በመጥላትና በማስወገድ አንበቀላቸው፡፡ አንሠራቸው፤ እንፍታቸው፡፡ እኛም በጥላቻ አንታሰር፡፡ ይልቁን በመባረክና ስለ እነርሱ በመማለድ እንፈታ፡፡ ያን ጊዜ ነገራችን ሁሉ ይለቀቃል፡፡
ሰዎችን ይቅር የማንል ከሆነ እግዚአብሔርም ኃጢአታችንን ይቅር አይልም፡፡ ኃጢአታችን ይቅር ካልተባለ ደግሞ የጸሎት መልሳችን ይያዛል (ማር 11፡25-26)፡፡ በአንድ ወቅት በአሜሪካን ሀገር እግዚአብሔር በፈውስ ሥጦታ ይጠቀምበት የነበረ ጆን ዋይምበር የተባለ ሰው ዘንድ እንዲጸለይላት አንዲት በጨጓራ በሽታ ትሰቃይ የነበረች ወጣት መጣች፡፡ እጁን ጭኖ ሲጸልይላት የጌታ መንፈስ ‹‹እናቷ›› የሚል ድምጽ አመጣለት፡፡ የጨጓራ በሽታና እናቷ ምን ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚችል ስላልገባው ጸልዮ አሰናበታት፡፡ ልጅቷ ግን ከበሽታዋ ስላልተፈወሰች እንደገና በሌላ ቀን ለጸሎት ወደ አገልጋዩ መጣች፡፡ ሲጸልይላት ሳለም አሁንም በድጋሚ የጌታ መንፈስ ‹‹እናቷ›› የሚል ድምጽ አመጣለት፡፡ በዚህን ጊዜ ጸሎቱን አቆመና ልጅቷን ስለ እናቷ ጠየቃት፡፡ እሷም በመበሳጨት ‹‹የእናቴን ነገር አታንሳብኝ፤ በጣም ራስ ወዳድ ሴት ናት፤ አልወዳትም፤በአምስት ዓመቴ ነው ጥላኝ የጠፋችው፤ በብዙ ሥቃይ ነው ያደግሁት፤ ስለዚህ እጠላታለሁ፡፡ ስለ እርሷ እንዲነሳብኝም አልፈልግም›› አለችው፡፡ ይህም የእግዚአብሔር ሰው ይቅር ማለት እንዳለባትና ይህን ባታደርግ ግን የእርሷም በረከት (ጤንነት) እንደማይለቀቅ ነገራት፡፡ከብዙ ትግል በኋላ ልጅቱ የአገልጋዩን ምክር ሰምታ እናቷን ይቅር አለች::ከዚያ አገልጋዩ ሲጸልይላት ወዲያሁኑ ልትፈወስ ችላለች::ለዚህ ነው የእግዚአብሔር ቃል ‹‹እናንተ ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም›› በማለት የሚያስጠነቅቀን (ማር 11፡26)፡፡
4.           ማንኛውም ክፉ ሃሳብ
የተለያዩ ክፉና ንጹህ ያልሆኑ ሃሳቦች ከወደቀው ሥጋችን (አዳማዊ ባሕሪያችን)ወይም ከክፉ መናፍስት ወደ አእምሯችን ሊላኩ ይችላሉ፡፡ የመጣውን ሃሳብ ሁሉ ማሰላሰል የለብንም:፡ ክፉና መጥፎ አሳቦችን ወዲያውኑ ልናስወግዳቸው ይገባል፡፡ በእርግጥ አእምሮን እንዳያስብ ማድረግ አይቻልም፤ ነገር ግን ቃሉ ማሰብ የሚገቡንን ነገሮች በተመለከተ እንዲህ ይለናል‹‹ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን እነዚህን አስቡ›› (ፊልጵስዮስ 4፡8):: ‹‹ወፎች ከራስህ በላይ እንዳይበሩ ልታግዳቸው አትችልም፤ ነገር ግን ጎጇቸውን በራስህ ላይ እንዳይሠሩ ልትከለክላቸው ትችላለህ›› ይላል የምዕራባውያን ብሂል፡፡ በመሆኑም የተለያዩ ሃሳቦች ከጠላትም ከየትም ወደ አእምሯችን ሊላኩ ይችላሉ፤ መጠንቀቅ ያለብን ጉዳይ ተቀብለን ማሰላሰልና በአእምሯችን ስፍራ መስጠት የሌለብን መሆኑን ነው፡፡ ይህን ማድረግ በራሳችን ላይ ዓመጽና እርኩሰት ሌላም ከንቱ የማያንጽ ሃሳብ ጎጆ እንዲሠራ ፈቀድን ማለት ነው፡፡ አሳባችን እንዳይፋንን ራሳችንን ልንገዛ ይገባል፡፡ የተሠጠን የማሰብ ችሎታ ፍሬ ከርሲኪውን ሁሉ እንድናስብ ልቅ እንዲያደርገን ልንፈቅድለት አይገባም፡፡ጤናማውንና የሚያንጸውን ብቻ ልናስብና ልናሰላስል ይገባል::
5.                ሐዘንተኛ ልብ
ሁል ጊዜ የሚተክዝ ልብ ለሰይጣን ይመቻል፡፡ ቃሉ ‹‹ሁል ጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ›› (ፊል 4፡4) ይላል፡፡ የጌታ ደስታ ልባችንን ሊሞላው ይገባል፡፡‹‹የእግዚአብሔር ደስታ ኃይላችሁ ነውና››  (ነህምያ 8፡10)፡፡ የእግዚአብሔር የሆነው ደስታ ወደ ልባችን ሲገባ ኃይልን እንሞላለን፡፡ ጌታ ኢየሱስ ወደ ምድር ከመጣባቸው ምክንያቶች አንዱ ‹‹በሐዘን መንፈስ ፋንታ የምስጋናን መጎናጸፊያ፤ በልቅሶ ፋንታ የደስታን ዘይት›› (ኢሳ 61፡3) ሊሠጠን ነው፡፡ በመሆኑም ዘመናችንን ሁሉ በመተከዝ ዕድሜያችንን በሰይጣን ማስዘረፍ የለብንም፡፡
ሰይጣን ትናንት ስለ ሠራነው ስህተትና ስለ ደረሰብን ችግር ዛሬ እያስተከዘ ዛሬን ይቀማናል፡፡ ይህ የጠላት ስልት ነው፡፡ ዛሬን ሳናጣጥም ነገ ይመጣብናል፡፡ ቃሉ ‹‹እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት፤ሐሴትን እናድርግበእርስዋም ደስ ይበለን፤" (መዝ. (118):24) ይላል፡፡ አንድ ሰው እንዲህ አለ፡- ‹‹90% ትኩረታችንን ማድረግ ያለብን በዛሬ ላይ ወይም ዛሬ ልንሠራቸው ባሰብናቸው ነገሮች ላይ ሊሆን ይገባል፤ 5% ደግሞ ስለ ትናንት በማሰብ ከስህተታችን ልንማር ከመልካም ተሞክሯችንም ልንበረታታ እንችላለን፡፡5% ደግሞ ስለ ወደፊት ሕይወታችን የምንተልምበት ሊሆን ይገባል::›› ሰይጣን ግን ከዚህ በተቃራኒ 90% ስላለፈው ውድቀታችንና ስህተታችን በማሰብ በጸጸት እንድንቃጠልና በተስፋ መቁረጥ እንድንሞላ ሊያደርገን ይፈልጋል፡፡ ብዙ ቅዱሳን ትናንት ያመለጣቸውን ዕድል በማሰብ፣ በትናንት ላይ ቆመው በመተከዝ ዛሬ ሊያደርጉ የሚገባቸውን ሳያደርጉ ፍሬ አልባ ሕይወት እየመሩ ይገኛል::የሰይጣንን ዘዴ ልንነቃ ይገባል:: 
እግዚአብሔር ኢያሱን ‹‹ባሪያዬ ሙሴ ሞቷል፤አሁንም አንተና ይህ ሕዝብ ተነሥታችሁ….ተሻገሩ››አለው (ኢያሱ 1፡2)፡፡ ስለ ትናንትው የሙሴ ታሪክና ገድል ቆሞ ማሰብ ለኢያሱም ሆነ ብዙ አሕዛብን ድል ነሥቶ የተስፋይቱን ሀገር የመውረስ የቤት ሥራ ላለበት የእስራኤል ሕዝብ አንዳችም የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ ሁል ጊዜም ሕያው ሆኖ ከሚኖረው ጌታ ጋር የዛሬውን የእግዚአብሔር አጀንዳ ለመፈጸም ልንተጋ ይገባል፡- ‹‹በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ›› (ፊልጵስዩስ 3፡11)፡፡ ያለፈውን ታሪክ ብቻ በመዘከር መኖር የለብንም፡፡ ጌታ ለእኛና ለቤታችንለቤተ ክርስቲያናችንና ለምድራችን ያለውን የዛሬ አጀንዳና ፈቃድ እያስተዋልን በጌታ ጸጋ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል፡፡ ያን ጊዜ ነው ጸጸት የሌለበት ሕይወት የምንመራው፡፡እግዚአብሔር ኩብኩባና ተምች የበላቸውን ዓመታት ሊያድስ ይችላል(ትን ኢዮኤል 2:25)::‹‹ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም›› (ኤር 29፡11)፡፡ ‹‹በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንዲፈጽመው ይህን ተረድቻለሁና›› (ፊል 1፡6)፡፡ ስለዚህ መስቀሉ ሥር ተንበርክከን ሐዘናችንንትካዜያችንንና ጸጸታችንን በጌታ ላይ ጥለን ጌታን ለማመስገንና ለማክበር እንነሳ፡፡ ትካዜያችንን በእግዚአብሔር ላይ ስንጥል ጌታ ይደግፈናል (መዝ 55፡22)፡፡
ሁልጊዜ የሚተክዝ ልብ ለጠላት ሥራ የተመቸ ነው::በአንጻሩ በመንፈስ ቅዱስ ደስታ የተፍለቀለቀ ሰው ሌሎችን ወደ ጌታ የመሳብ ኅይል አለው::የመስቀሉ ሥራ የሃዘናችንን ቀንበር ሊሰብር ይችላል::ጌታ በመስቀል ላይ ሲሞት ስለ እኛ ሁሉን ዕዳ ከፍሏል::በጌታ ደስ ይበለን::
  6.              ትዕቢት
“እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፣ ለትሑታን ግን ጸጋ ይሰጣል” (ያዕቆብ 4፡6)፡፡ "ትዕቢትን" በሁለት መልክ ልናየው እንችላለን፡፡
1) "ትዕቢት" የእግዚአብሔርን ቃል አለመስማት /አለመታዘዝ/ ነው የጌታን ቃል መናቅ ትዕቢት ነው (ዘዳግም 1፡43)፡፡ በአንፃሩ ትሕትና ደግሞ ለእግዚአብሔር ቃል መንቀጥቀጥ (መታዘዝ) ነው፡- “ወደዚህ ወደ ትሑት በቃሌም ወደ ሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ” (ኢሳ 66፡2)፡፡ 2)ሌላው የትዕቢት መገለጫ ሌሎችን መናቅ ነው፤ማለትም ራስን አግዝፎ ማየትና ሌሎችን አሳንሶ ማየት ነው፡፡ የትዕቢት ኃጢአት ስውርና እንዴት እንደያዘን ሳይታወቅ የሚሰለጥንብን በመሆኑ ሁልጊዜ ራሳችንን ባዶ በማድረግ በትሕትና ለመመላለስ መጣር አለብን፡፡ ቃሉ “በጊዜው ከፍ እንዲያደርገችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ” ይላል(1ኛ ጴጥ 5፡6)፡፡  “ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፣ ራሱንም የሚያዋርድ ከፍ ይላል” (ሉቃ 14፡11) በማለት ቃሉ ያስጠነቅቀናል፡፡ በአንድ ሥፍራ እንዲህ የሚል አባባል ማንበቤ ትዝ ይለኛል፡- “እኛ የራሳችንን ሥራ ካልሰራን (ራሳችንን ካላዋረድን) እግዚአብሔር የእኛን ሥራ ይሠራል (ያዋርደናል)፡፡" ራሳችንን ማዋረድ የእኛ ድርሻ ሲሆን ከፍ ማድረግ ደግሞ የጌታ ድርሻ ነው::
ጌታ ኢየሱስ ራሱን ባዶ በማድረግ ሰው ሆነ:: ዝቅተኛውን ሥፍራ ወሰደ በበረት ተወለደ በእንጨት ላይ ተሰቀለ እግዚአብሔር ግን ያለ ልክ ከፍ ከፍ አድረገው “ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው” (ፊልጵስዩስ 2፡9)፡፡ ራሳችንን ስናዋርድ እግዚአብሔር ያከብረናል፡፡ የእግዚአብሔር ቤት የትዕቢተኞች ቤት ሊሆን አይገባም፤የትሁታን ቤት እንጂ፡፡ ስለዚህ ሁል ጊዜ በጌታ ፊት ራሳችንን ማዋረድ አለብን፡፡ እርስ በርስም በትሕትና ልንከባበርና ባልንጀራችን ከእኛ እንዲሻል ልንቆጥር ይገባል፡፡ ቃሉ “ዓይኖቼ በምድር ምዕመናን ላይ ናቸው፣ በቀና መንገድ የሚሄድ እርሱ ያገለግለኛል፣ ትዕቢትን የሚያደርግ በቤት መካከል አይኖርም”ይላል (መዝ 101፡6-7) ፡፡ መዘንጋት የሌለበን ትዕቢት ሰይጣን እራሱ የወደቀበት ኃጢአት መሆኑን ነው (ኢሳ 14፣12-16)፡፡ በምንታበይበት ጊዜ በሰይጣን የአሠራር መርህ ውስጥ እንገባለን፡፡ ስለዚህ ሁል ጊዜ ከትዕቢት እንጠንቀቅ፤ እግዚአብሔርም እንዲረዳን እንጸልይ:: “እግዚአብሔር ከፍ ያለ ነውና ወደ ችግረኞች ይመለከታል፣ ትዕቢቶኞችንም ከሩቅ ያውቃል” (መዝ 138፡6)፡፡
7.              ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ቁጣ
 “ተቆጡ ግን ኃጢአት አታድርጉ” (መዝ 4፡4) ይላል ቃሉ፡፡ በሌላ ስፍራ ደግሞ ‹‹በቁጣችሁ ላይ ጸሐይ አይግባ፥ለዲያቢሎስም ፈንታ አትስጡት›› (ኤፌ4፡25) ይላል፡፡ መቆጣት በራሱ ኃጢአት አይደለም፤ ነገር ግን ቁጣ ወደ ንዴት፣ ብስጭትና ኩርፊያ ሲሄድ ግን ኃጢአት ይሆናል፡፡ በምንበሳጭበት ጊዜ ወይም መራራ ቁጣ በምንቆጣበት ጊዜ ውስጣችን የሚያድረው የእግዚአብሔር መንፈስ ያዝናል፡፡ በመሆኑም በምንቆጣበት ጊዜ ራሳችንን ልንገዛ ይገባል፡፡ አንደበታችንን ልንገራ ይገባል፡፡ እንደዚያ ሲሆን ጠላት ዕድል ፈንታ ያጣል፡፡መራራነትና ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ቁጣ መንፈስ ቅዱስን ከማሳዘኑ በተጨማሪ ለሰይጣን በር ይከፍታል::"ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ::መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ::"(ኤፌሶን 4:30-31)
8.                 ዓመፅ
ለሰይጣን በሕይወታችን በር የሚከፍተው ሌላው ዓመፀኝነት ነው፡፡ ለተለያዩ የሥልጣን ተዋረዶች ልንገዛ ይገባል፡፡ ልጆች ለወላጆቻቸው ሚስት ለባሏተማሪ ለአስተማሪአስተማሪ ለርዕሰ መምህሩየጸሎት አገልጋይ ለጸሎት ቡድን መሪውምዕመናን ለመጋቢው ወይም ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሊታዘዙ ይገባል፡፡ የሥልጣን ተዋረድ መኖር ከብጥብጥ ይጠብቃል፡፡ ከሥልጣን ክፍተት የተነሣ ሶማሊያ ውስጥ ያለውን ብጥብጥውከትና ያስከተለውን መዘዝ ስንመለከት የሥልጣን ጠቃሚነት ይገባናል፡፡ ዓመፅ ሕይወታችንን እንዳይገዛው ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡
ዓመፀኛ የሆኑ ሰዎች በየደረሱበት ከኃላፊዎች ጋር የመጣላት ዝንባሌ አላቸው፡፡የሥራ ኅላፊን እንደ ባላንጣ የማየት ዝንባሌ ይታይባቸዋል::በየደረሰበት መሥሪያ ቤት ከአለቆች ጋር የሚጣላ ሰው ዓመፀኛ መሆኑን ልንጠራጠር አይገባም፣ እንደዚህ ዓይነቱ ሰው ለሥልጣን መታዘዝ የሚቸገር ሰው ነው:: እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ከህፃንነት ጀምሮ ለሥልጣን የመታዘዝ ክፍተት የገጠማቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ምናልባት ወላጆች የሌላቸውና ቢኖሯቸውም ተገቢውን ሥርዓት (discipline) ሳያስይዙ ያሳደጓቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ሰይጣን ራሱ ዓመፀኛ መሆኑን ልንዘነጋ አይገባም፡፡ ለእግዚአብሔር አልገዛም ብሎ ያመፀ ነው፡፡ አጋንንትም እንደዚሁ ከእርሱ የዓመፅ ጎራ የተሰለፉ ናቸው፡፡ ሰይጣንም በዓመፁ ምክንያት የነበረውን ሥፍራ አጥቷል፡፡(ትን ኢሳ 14:12-15፤ትን ሕዝ 28:11-18፤ራእይ 12:7-10)
በምናምጽበት ጊዜ በሰይጣን የአሠራር ጎራ ውስጥ እንገባለን፡፡ ዳታንና ቆሬ በሙሴ ላይ ያመፁትን ዓመፅ እግዚአብሔር አልታገሰውም፡፡ተቀጥተዋል::ስለዚህ ዓመፅን ልንጸየፍ ይገባል፡፡
9.   እኔነት
ሌላው የሰይጣን መቆሚያ እኔነት ነው፡፡ ራስ ወዳድነትየራስን ክብር መፈለግና ራስ ተኮር ብቻ የሆነ የሕይወት አካሄድ ለሰይጣን አሠራር የሚመቹ ክፍተቶች ናቸው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ራሳችንን በመካድ መስቀላችንን ተሸክመን እንድንከተለው አዞናል፡፡ ራሳችንን ስንክድ ብቻ ነው በእውነት እግዚአብሔርን የሚያስከብር ኑሮ መኖር የምንችለው፡፡ 24 ሰዓት ሙሉ ስለ ራሳችን ብቻ እንድናስብ አልተጠራንም፡፡ እግዚአብሔር ከራስ ወዳድነት እንዲገላግለን እንለምነው፡፡ ያን ጊዜ የተትረፈረፈውን ሕይወት መኖር እንጀምራለን፡፡ ለሌሎች መኖር ስንጀምር ሕይወት ጣዕም ይኖራታል፡፡ ራስን መውደድ ኃጢአት ባይሆንም እንኳን ሌሎችንም እንደ ራሳችን እንድንወድ ታዘናል፡፡ ራስን መውደድ ኃጢአት አይደለም፡፡ ራስ ወዳድነት /selfishness/  ግን ኃጢአት ነው፡፡ “ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶች ሆነው ይመላለሳሉ፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፣ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ፤መጨረሻቸው ጥፋት ነው፤ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፤ ክብራቸው በነውራቸው ነው፤ ሃሳባቸው ምድራዊ ነው” (ፊልጵስዩስ 3፡18-19)፡፡
ከላይ የተዘረዘሩት 9 ነገሮች ሰይጣን ወደ ሕይወታችን ክፉ ተጽዕኖ እንዲያመጣ መንገድ ሊሆኑ የሚችሉ በመሆናቸው ከሕይወታችን ልናስወግዳቸው ይገባል፡፡ከመንፈስ ፍሬ ጋር የሚቃረኑ የሥጋ ስራዎች ሁሉ ሰይጣን በሕይወታችን ሥፍራ እንዲያገኝ የሚያግዙ ናቸው (ገላትያ 5:16-24):: የሰይጣንን መግቢያ ከእነዚህ አቅጣጫ ከዘጋንየእሱን ክፉ ተጽ ዕኖ ሁሉ ከሕይወታችን ማራቅና የድል ሕይወት መምራት እንችላለን፡፡
ለ. በምስጋናና ውዳሴ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ
ጠላትን የመዋጊያው ሌላው ስልት ደግሞ በምስጋናና በውዳሴ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ነው፡፡ “ከሕፃናትና ከሚያጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀ ስለጠላትህ፣ ጠላትንና ቂመኛን ለማጥፋት” (መዝ 8፡2) ይላል ቃሉ፡፡ “ቅዱሳን በክብር ይመካሉ፤ በምንጣፋቸውም ላይ ሐሴትን ያደርጋሉ፡፡ የእግዚአብሔር ምስጋና በጉሮሮአቸው ነው፡፡ ሁለት አፍ ያለው ሰይፍ በእጃቸው ነው በአሕዛብ ላይ በቀልንበሰዎችም መካከል ቅጣትን ያደርጉ ዘንድንጉሦቻቸውን በሰንሰለትአለቆቻቸውንም በእግር ብረት ያስሩ ዘንድየተጻፈውን ፍርድ ያደርጉባቸው ዘንድ ለቅዱሳን ሁሉ ይህች ክብር ናት፤ ሃሌሉያ›› (መዝ 149፡5-9)፡፡“ምስጋናን የሚሰዋ ያከብረኛልየእግዚአብሔርን ማዳን ለእርሱ የማሳይበት መንገድ ከዚያ አለ::” (መዝ 50፡23) “እንግዲህ ዘወትር ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ በእርሱ እናቅርብለት” (ዕብ 13፡15)፡፡  
እግዚአብሔርን ስለ ታላቅነቱ ልንወድሰው ይገባል፤ ስለቸርነቱ ልናመሰግነው ይገባል፤ አንደበታችንን በመክፈት “ትልቅ ነህኃያል ነህኤልሻዳይ ነህ ታማኝ ነህንጉሥ ነህጌታ ነህአምላክ ነህእፁብ ድንቅ ነህክቡር ነህ ቅዱስ ነህየሚመስልህ የለምየነገሥታት ንጉሥ ነህማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ውስጥ ትኖራለህመጀመሪያና መጨረሻ አልፋና ኦሜጋ ነህ" ልንለው ይገባል፡፡ በሌላም ብዙ ቃላትና ዜማ ልናወድሰው ይገባል፡፡ ይህ ውዳሴያችን ለጌታ ጣፋጭ መሥዋዕት ሲሆን ለሰይጣን ግን መራራ ነውአስደንጋጭ ነው፡፡
በተጨማሪም እግዚአብሔር ስላደረገልን ነገር ዘወትር ልናመሰግነው ይገባል፤ “ልጅህ ስላደረግኸኝ አመሰግንሃለሁ፤ በጌታ በኢየሱስ ሞትና ትንሳኤ ዳግም ልደትን ስለ ሰጠኸኝ ተመስገን፤የዘላለም ሕይወት ስላገኘሁና ስሜን በሕይወት መጽሐፍ ስለ ጻፍከው ክበር ተመስገን፤ከዘላለም ሞት ስላዳንከኝ ተመስገን፤ከሰይጣን የጨለማ መንግሥት ወደ ልጅህ የፍቅር መንግሥት ስላፈለስከኝ አመሰግንሃለሁ፤ኃጢአቴን ሁሉ ይቅር ስላልከኝ ተመስገን፤ በጌታ በኢየሱስ ክቡር ደም ስላነፃኸኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ስለሞላኸኝ ተመስገን፤ኃይልንና ብርታትን ስላበዛህልኝ ተመስገን፤ስለ ሰጠኸኝ ጤንነት ተመሰገን፤ስለ ሰጠኸኝ ቤተሰብ ተመስገን፤ አንተ ፈዋሼ ነህ፤ ብርሃኔ ነህ፤መድሐኔቴ ነህ፤ክብሬ ነህ፤ምስጋናዬ ነህ፤ተስፋዬ ነህ፤ጌታዬ ነህ፤ሰላሜ ነህ፤አምላኬ ነህ፤ጉልበቴ ነህ፤እረኛዬ ነህ፤መታመኛዬ ነህ፤ ዕረፍቴ ነህ፤ጥበቤ ነህ፤ንጉሤ ነህ፤ጽድቄ ነህ፤ኃይሌ ነህ›› ልንለው ይገባል፡፡
በምስጋናና ውዳሴ የተሞላ ሕይወት የሚመራ ክርስቲያን ለጠላት ድንጋጤ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ወደ እግዚአብሔር ፈት በምንቀርብበት ጊዜ ሁል ጊዜ በውዳሴና በምስጋና መቅረብ ተመራጭ መሆኑን አንዘንጋ፡፡
ሐ. ቃሉን ማንበብና ማሰላሰል
የእግዚአብሔር ቃል የመንፈስ ሰይፍ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ እኔ የነገርኳችሁ ቃል መንፈስ ነውሕይወት ነው (ዮሐ 6፡63) ብሏል፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ስናነብ ወይም ስንሰማ የቃሉ መንፈስ ወደ ሕይወታችን ይገባል፤ በጎ ተጽዕኖ ይፈጥርብናል፡፡ እምነትን በውስጣችን ይፈጥራል፡፡ በቃሉ ውስጥ የእግዚአብሔርን ድምፅ ለሁኔታችን እንሰማለን፡፡
አእምሯችን ሥራ መፍታት የለበትም፤ ቃሉን ማሰላሳል አለብን፡፡ ‹‹ሰው በልቡ እንዳሰበ እንደዚሁ ነውና›› (ምሳሌ 23፡6) ይላል ቃሉ፡፡ የሽንፈት ሃሳብ የምናስብ ከሆነ ተሸናፊዎች እንሆናለን፡፡ የድልን ሃሳብ የምናስብ ከሆነ ድል እናደርጋለን፡፡ ስለዚህ ማሰላሰል ያለብን የአግዚአብሔርን ቃል ነው፡፡ የአስተሳሰብ ክፍላችንን በእግዚአብሔር ቃል እንሙላው፡፡ ከተቻለም ተንበርክከን እናንብበው፡፡ በየቀኑ 4 ምዕራፎችን ብናነብመጽሐፍ ቅዱሳችንን  በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንጨርሳለን፡፡ በየእለቱ ስምንት ምዕራፍ ካነበብን ደግሞ በ 6 ወር መጽሐፍ ቅዱሳችንን አንብበን መጨረስ እንችላለን፡፡ አዲስ ኪዳን 260 ምዕራፎች አሉት፡፡ በየእለቱ 10 ምዕራፎችን ብናነብአዲስ ኪዳናችንን በ26 ቀናት ውስጥ መጨረስ እንችላለን፡፡በየዕለቱ ከአዲስ ኪዳን 5 ምዕራፍ ብናነብ ደግሞ በ2 ወር ጊዜ አዲስ ኪዳንን አንብበን መጨረስ እንችላለን፡፡
አሉታዊ ነገሮችን በመስማት ጊዜያችንን የምናጠፋ ከሆነ ለሰይጣን በር እንከፍታለን፡፡የምንሰማቸውየምናነባቸውና የምናያቸው ነገሮች በጎ ወይም አፍራሽ ተጽእኖ በሕይወታችን ላይ የመፍጠር ዓቅም አላቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል  ይሻለናል፡- የቅድስና ተጽእኖ ይፈጥርብናልየበጎ ነገር ተጽእኖ ይፈጥርብናል፡፡ ‹‹የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ›› (ቆላ 3፡16)፡፡
የእግዚአብሔርን ቃልና መንፈሳዊ መልዕክቶችን የምናነብና የምንሰማ ከሆነ የታደሰ አእምሮ ይኖረናል፡፡ እግዚአብሔር የታደሰ አእምሮ ባለው /ባላት ክርስቲያን ሕይወት በጣም ይጠቀማል፡፡ አንድ ሰው ‹‹ዳግም የሚወለደው መንፈሳችን ነው፤ አእምሯችን ግን ይታደሳል›› ብሏል፡፡ አእምሯችን ከአሮጌው አስተሳሰብና ከኃጢአተኝነት የሚላቀቀው በእግዚአብሔር ቃል ሲታደስ ነው፡፡ ሰውን ለመቀየር ከፈለግን አስተሳሰቡን መቀየር አለብን፡፡ የሰው አስተሳሰብ በእግዚአብሔር ቃል ሲቃኝና ሲታደስ አስተሳሰቡ የተለወጠ ሰው ይሆናል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል፡- "የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሳፅ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል" (2ኛጢሞ 3፡16-17)፡፡
ብዙ አማኞች በዳግሞ ልደት አዲስ ሕይወት አግኝተዋል፡፡ ሆኖም ግን አስተሳሰባቸው እንደ ቀድሞው አሮጌ ነውአልታደሰም፡፡ እንደ ድሮ ያስባሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለጠላት በር ይከፍታል፡፡ "ሰው በልቡ /አእምሮው/ እንዳሰበው እንዲሁ ነውና" (ምሳሌ 23፡6) :፡ ስለዚህ እንደ እግዚአብሔር ቃል እናስብ::ደግሞም እንደ እግዚአብሔር ቃል እንናገር፡፡ ያን ጊዜ ሰይጣን ዕድል ፈንታ በሕይወታችን ውስጥ ያጣል፡፡
መ. መቀደስ
የተቀደሰ ሕይወት ለጠላት ጸር ነው፡፡ በተቀደሰ ሕይወት ውስጥ ሰይጣን ዕድል ፈንታ አይኖረውም፡- ‹‹እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ›› ብሏል ጌታ(ዘሌዋውያን 19፡2)፡፡ የተቀደሰ ሕይወት ለጌታ መጠቀሚያ ይሆናል፡፡ የአስተሰሳብየንግግርና የአካሄድ ቅድስና ሲኖረን ጌታ በሕይወታችን ይከብራል፡፡ ዕለት ዕለት ለመቀደስ መፈለግ አለብን፡፡ ‹‹ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፤ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና›› (ዕብራውያን 12፡14)፡፡
 ሠ. በልብ አንድነት መጸለይ ወይም ኅብረት ማድረግ (መዝ 133፡ 1-3፣ ሮሜ 15፡5፣ ኤፌ 4፡3፣ ቆላ 3፡14)
በአንድ ልብ መጸለይና ኅብረት ማድረግ በጠላት ላይ ድልን ለማግኘት ዓይነተኛ መንገድ ነው፡፡ ሰይጣን ‹‹ከፋፍለህ ግዛ›› የሚለውን የቀድሞ ቅኝ ገዢዎች መርህ በጣም ይጠቀማል፡፡ የልብ አንድነታችንና ጤናማ ኅብረታችንን በእጅጉ ይዋጋል፡፡ በአንድ ልብ ስንሆን ጸሎታችን ስለሚሰማ ለጠላት ሥራ ትልቅ እንቅፋት እንሆናለን፡፡ በአንድ ልብ ስንጸልይ መንፈሳዊ ጉልበታችን ስለሚጨምር የጠላት ኃይልና ሥራ ይፈርሳል፡፡ ‹‹አንዱ ሺህ ሁለቱ አስር ሺህ ያሳድዳሉ›› ይላል ቃሉ(ዘዳግም 32፡30)፡፡ በአንድ ልብ ስንሆን ከመደመር ስሌት ወጥተን ወደ ብዜት ስሌት ወይም ወደ ስኬት የምንገባው፡፡ አንድ ልብ እንዲኖረን የተቻለንን ሁሉ ጥረት ልናደርግ ይገባል፡፡ በአንድ ልብ መጸለይበአንድ ልብ ማገልገልና በአንድ ልብ አብሮ መኖር የድል ሕይወት መለማመጃ ምስጢር ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል “እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ” ይላል(ገላትያ 5፡15)፡፡ የልብ አንድነት አለመኖር ለጠላት ሥራ አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ በመሆኑም በመቀባበልበመከባበርና በትሕትና የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ሁላችንም የበኩላችንን ድርሻ ልንወጣ ይገባል፡፡ ይህም በመንፈሳዊ ውጊያ ባለድል ያደርገናል፡፡
ረ. የኢየሱስ ስም
“የእግዚአብሔር ስም የጸና ግንብ ነውጻድቅ ወደ እርሱ ሮጦ ከፍ ከፍ ይላል” (ምሳሌ 18፡10) ፡፡ ጠላትንና ሥራውን ለማፍረስ የጌታ ኢየሱስን ስም በእምነት ልንጠራው ይገባል፡፡ ስሙ ዓለታችን ነው፡፡ ስሙን ጠርተን አናፍርም፡፡ ከስም ሁሉ በላይ የሆነ ስም ስለሆነ በጠላት ኃይል ላይ ፈጥኖ ከአንደበታችን ሊወጣ የሚገባ ስም ነው፡፡ ቃለ እግዚአብሔር ‹‹የአምላክህን የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ አትጥራ›› (ዘጸ 20፡7) ስለሚል የጌታን ስም ስንጠራ በአክብሮት ሊሆን ይገባል፡፡
ሰ. የኢየሱስ ደም
በዕብራውያን 11፡28 ላይ “አጥፊው የበኩሮችን ልጆች እንዳይነካ ፋሲካንና ደምን መርጨትን በእምነት አደረገ” ይላል፡፡ እኛ ካህናት ነን (1ኛ ጴጥሮስ 2፡9፣ራእይ 1፡6)፤ የጌታን የኢየሱስን ደም በእምነት በቤታችን ላይ ልንረጭ ይገባል፡፡ የጌታ ደም የዘላለም ኪዳን ደም ነው፡፡“ከበጉ ደምና ከምስክርነታቸው ቃል የተነሳ  ድል ነሱት” ይላል ቃሉ(ራእይ 12፡11) ፡፡
መንፈሳዊ ውጊያ ስናደርግ ከላይ የተዘረዘሩትን የውጊያ ስልቶች ብንከተል እጅግ ውጤታማ እንሆናለን::"ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል"(ትን ሆሴዕ 4:6) እንደሚል ቃሉ ለመንፈሳዊ ውጊያ ተገቢው መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውቀት ያስፈልገናል::ስለ መንፈሳዊ ውጊያ ስናስብ "በኢየሱስ ስም" ብቻ ማለት እንደሆነ ልናስብ አይገባም::ለጠላት ሥፍራ ሰጥተንበኢየሱስ ስም ስንል ብናድር ምንም ለውጥ ላይመጣ ይችላል::ለጠላት የከፈትነውን በር መጀመሪያ መዝጋት አለብን::ሌሎችንም የውጊያ ስልቶች ማለትም፥በምስጋናና በውዳሴ መቅረብ፥ቃሉን ማንበብና ማሰላሰል፥መቀደስ፥በአንድ ልብ መጸለይና የኢየሱስን ደም በመንፈሳዊ ውጊያ ውስጥ ልንጠቀም ይገባል::  
V.                                  መንፈሳዊ ውጊያና የመንፈስ ቅዱስ ምሪት
መንፈሳዊ ውጊያ ስናካሂድ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ሊሆን ይገባል፡፡ ከመንፈስ ቅዱስ ውጪ መንፈሳዊ ውጊያ ማድረግ የለብንም፡፡ “ጠላትህን ከፊትህ አውጥቶ አጥፋው ይላል” (ዘዳ 33፡27) እንደሚል ቃሉ መንፈስ ቅዱስ የሚጠቁመንን ጠላት ልናጠፋ ይገባል፡፡ ነፋስ እንደሚጎስም መዋጋት የለብንም፡፡ ጌታ የተለመልንን ውጊያ ልንዋጋ ይገባል፡፡ ምድራዊ የሆነ ጦርነት ለማካሃድ እንኳ ዳዊት የጌታን ምሪት ይጠይቅ ነበር፡፡ ኢያሱንም ስንመለከት በጌታ ምሪት ነበር የሚዋጋው፡፡ መንፈሳዊ ውጊያ ደግሞ ከዚያ እጅግ የረቀቀና የጌታ ምሪት ሙሉ ለሙሉ የሚያስፈልገው ነው፡፡  
ዳዊት የጌታን ምሪት ጠይቆ ለጦርነት ይወጣ ስለነበር በሄደበት ሁሉ እግዚአብሔር ድል ይሰጠው ነበር (2ኛ ሳሙ 2፡1)፡፡ ጌታ ኢየሱስ “እውነት እላችኋለሁ፣ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልምያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና ” ብሏል(ዮሐ 5፡19)፡፡ ጌታ ኢየሱስ ሁል ጊዜ በእያንዳንዱ ነገር ከአባቱ ሰምቶ የአባቱን ፈቃድ ብቻ ያደርግ እንደነበር ሁሉእኛም መንፈሳዊ ውጊያ ስናደርግ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡ “ እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል” (ዮሐ 16፡1) ይላል ቃሉ፡፡
"ያለ ጌታ ምሪት ያደረጉት ውጊያ ብዙ ዋጋ እንዳስከፈላቸው ከባለቤታቸው ከፓስተር ኤዲ እስሚዝ ጋር የአሜሪካው  የጸሎት ማዕከል መስራች የሆኑት ዶ/ር አሊስ እስሚዝ ከጥቂት ዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ለአገልግሎት በመጡ ጊዜ የሚከተለውን መስክረውልናል፡-
በምኖርበት የዩስተን ከተማ ገዢ የሆኑት መናፍስት የትኞቹ እንደሆኑ እንዲነግረኝ ጌታን በጸሎት ጠየኩት፡፡ ጌታም የስድስት ገዢ መናፍስትን ስሞች ጠቆመኝ፡፡ ከዚያም ወዲያውኑ ጾም ጸሎት በመያዝ ኮመናፍስቱ ጋር ውጊያ ገጠምኩኝ፡፡ ከዚያም በዚያ ዓመት ብቻ በቤተሰባችን ውስጥ ስድስት ሰዎች የቀዶ ጥገና ሕክምና በሚያስፈልገው ሕመም ተመታን፡፡ በሁኔታው ግራ በመጋባት ጌታን ‹‹ምነው ይሄ ሁሉ ሲሆንብን እያየህ ዝም አልከን?›› ብዬ ጠየኩት፣ ጌታም ‹የስድስቱን ገዢ መናፍስት ስም ጠየቅሽኝእኔም ነገርኩሽ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ምን ማድረግ እንዳለብሽ እኔን አልጠየቅሽኝምኮ ልጄ› አለኝ፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ የጌታን ምሪት ሳንጠይቅ እኔና ባለቤቴ ምንም ዓይነት መንፈሳዊ ውጊያ አናደርግም ለድላችን ቁልፉ ያለው ጌታን ሰምተን መዋጋቱ ላይ መሆኑን ከደረሰብን መንፈሳዊ ጥቃት ትምህርት ወስደናል፡፡"
የመናፍስት አሰራር ረቂቅ በመሆኑ በሥጋና በደም ልንረዳው አንችልም፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ምሪት እጅግ ያስፈገናል፡፡ የትኛውን መንፈሳዊ የጦር ዕቃ መቼ መጠቀም እንዳለብን ከጌታ ምሪት መቀበሉ አስፈላጊ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ በኢየሱስ ስም መቃወም ውጤታማ ሊያደርገን ይችላልሌላ ጊዜ ደግሞ በምስጋናና በውዳሴ ብቻ በጌታ ፊት መቅረብ ጠላትን ሊመታው ይችላል፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ ቃሉን በመጥቀስ መዋጋት ውጤታማ ሊያደርገን ይችላል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ የኢየሱስን ደም በመጥቀስና በእምነት በመርጨት መዋጋቱ ሊመረጥ ይችል ይሆናል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከወገናችን ጋር በአንድ ልብ ሆኖ መጸለይና ማምለክ የጠላትን ሥራ ለማፈራረስ ወሳኝ ይሆናል፡፡ ስለዚህ የትኛውን መንፈሳዊ የዉጊያ ስልት መቼ መጠቀም እንደሚገባን ጌታ እንዲመራን እንጠይቀው፡፡ ለጠላት መቆሚያ የሚሆኑ ነገሮችንም ከሕይወታችን ማስወገድ አንዱ ጠላትን የመቃወሚያው ዋና መንገድ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡
አንዳንድ ወገኖች ወደ ጠንቋይ ቤት ሄደው መንፈሳዊ ውጊያ ለማካሄድ እንደሞከሩ የሰማሁዋቸው ታሪኮች አሉ፡፡ ጌታ ብሏቸው ከሆነ የሄዱት መልካም ነው፤ በቅንአት ብቻ ተነሣሥተው ያለ ምሪት ከሄዱ ግን አላስፈላጊ ዋጋ ከመክፈል ውጪ  ውጤታማ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ “ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሳ ጠፍቶአል” (ሆሴዕ 4፡6) እንደሚል ቃሉ የእውነት እውቀት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ “የማያስተውል ሕዝብ ይገለበጣል” የሚለውን ቃል ልብ በማለት በመንፈሳዊ ማስተዋልና ጌታን በማድመጥ መንፈሳዊ ውጊያ ልናደርግ ይገባል፡፡ “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም፤ በዚያን ቀን ብዙዎች ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህስ አጋንንት አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንምን? ይሉኛል፡፡ የዚያን ጊዜም ከቶ አላወቅኋችሁም! እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ” (ማቴ 7፡21-23) በማለት ጌታ ያስጠነቅቀናል፡፡ ዋናውና ጠቃሚው ነገር አጋንንት ማውጣትትንቢት መናገር ወይም ብዙ ተአምራት ማድረግ ሳይሆን የአብን ፈቃድ ለይተን ማድረግ ነው፡፡
እነ ጳውሎስ ቃሉን እንዳይናገሩ መንፈስ ቅዱስ እንደ ከለከላቸው እናነባለን (ሐዋ 16፡6)፡፡ ከዚያም ወደ ቢታንያ ይሄዱ ዘንድ ሲሞክሩ የኢየሱስ መንፈስ አልፈቀደላቸውም፤ ከዚያም በራእይ እና በምሪት ወደ መቄዶንያ እንደሄዱ እንገነዘባለን፡፡ እነዚህ ሰዎች በሌላ ጊዜ ወደ እስያ ሄደው ወንጌል ሰብከዋል፡፡ መቼ ምን ማድረግ እንዳለብን ጌታ ምሪት ይሰጠናል፡፡ በአንድ ወቅት  የከለከለንን ነገር /ጊዜው ባለመሆኑ/ በሌላ ጊዜ ሊፈቅድልን ይችል ይሆናል፡፡ ስለዚህ ጌታን የሚሰሙ የተከፈቱ የልብ ጆሮዎች ያስፈልጉናል፡፡


ዎች ማን ኒ የተባሉ ቻይናዊ አገልጋይ ምሪትን በተመለከተ የሚከተለውን ብለዋል “እግዚአብሔርን የሚፈሩና ራሳቸውን የካዱ ሰዎች ጌታ ያልከለከላቸውን ነገር ሁሉ እንደ ተፈቀደ አስበው ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ፡፡ ጌታ የማይፈቅደውን ነገር በመከልከል ወይም ባለመፍቀድ የሚያሳውቃቸው ሲሆን ፈቃዱ የሆነውን ነገር ሲያደርጉ ግን ምንም የተዐቅቦ ድምፅ በውስጣቸው አይሰሙም፡፡ እነ ጳውሎስን ጌታ በዚህ መንገድ ነበረ የሚመራቸው፡፡” እንዲያው በዘፈቀደ እየተነሱ “ጌታ እንዲህ አለኝ” የሚሉ ሰዎችን ይህ አይመለከትም፡፡ እግዚአብሔርን ለሚፈሩ፣ ራሳቸውን ለካዱና የጌታን ፈቃድ ብቻ ለሚፈልጉ በዚህ ዓይነት መንገድ ሊመራቸው ይችላል፡፡ “ጌታ ሆይ ድምፅህን መስማትና መለየት አስተምረኝ” ብለን እንጸልይ፡፡ ጌታ ዳቦ ብንለምነው ድንጋይ አይሰጠንም፤ ዓሳ ስንለምነው እባብ አይሰጠንም፡፡ ድምጹን መለየት ያስተምረናል፣ ያሳድገናል፡፡ በቃሉ መሞላትና ከጌታ ጋር በጸሎት ሰፊ ጊዜ ማሳለፍ ድምጹን ለመለየት እጅግ ይጠቅማል፡፡ መንፈስ ቅዱስንም ዕለት ዕለት መሞላት የጌታን ድምፅ ለመለየት ይረዳል፡፡ ጌታ ጥበብንና ማስተዋልን እንዲሰጠንም በጸሎት ልንጠይቀው ይገባል፡፡ያን ጊዜ ስኬታማ የሆነ መንፈሳዊ ውጊያ ልናካሄድ እንችላለን::

Monday, July 15, 2013

አዋቂ ተኮር አገልግሎት ቢቀየርስ
በወ/ም ተድላ ሲማ
ሐዋሳ ከተማ ውስጥ በልጆች አገልግሎት ላይ ሸክም የነበረው አንድ ወንድም እንዲህ አለ፥"አይ ቤ/ክርስቲያን፥ ለሙን መሬት ትታ በጭንጫ ላይ ዘር በመዝራት ትደክማለች::" ይህ ሰው ይህን ያለው የአንዲት አጥቢያ ቤ/ክርስቲያን ምዕመናን ቤ/ክርስቲያን ውስጥ ተቀምጠው መንፈሳዊ ፕሮግራም ሲካፈሉ፥ ልጆቹ ግን ውጪ ፀሐይ ላይ ሲንቃቁ በማየቱ፥ለምን ትኩረት ተነፈጋቸው? በማለት ነበር::በርግጥ አዋቂዎችን በ"ጭንጫ" መመሰሉ ጠንከር ያለ አባባል ሊመስል ይችላል::ለአዋቂዎች የሚሰጠው ትኩረት ተገቢ አይደለም ለማለት አይደለም የዚህ ጽሑፍ ዓላማ፤ሆኖም ግን በቤ/ክርስቲያን ውስጥ የሚታቀዱት ፕሮግራሞች በአብዛኛው አዋቂ ተኮር መሆናቸውን ለማሳየትና ይህ አካሄድ እንዲስተካከል ለማስገንዘብ ነው::ከቤ/ክርስቲያን በጀት አብዛኛው አዋቂ ተኮር ለሆኑ ዕቅዶች እንጂ ልጆችን ያማከለ እንዳልሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነው:: ለመሆኑ የልጆች ኮንፍራንስ የሚል ሰምተን እናውቃለን? አብዛኛው የቤ/ክርስቲያን አገልጋዮች ጊዜና ጉልበት የሚባክነው አዋቂዎችን በማገልገል ነው ወይስ ልጆችን?የልጆች ቁጥር በአንዳንድ አብያተክርስቲያናት ከአዋቂው የማይተናነስ መሆኑም መዘንጋት የለበትም::
ቤ/ክርስቲያን ለልጆችና ለታዳጊ ወጣቶች የምትሰጠው ትኩረት በጣም ሊጨምር ይገባል::ይህ ካልሆነ ግን ከጥቂት ዓመታት በኋላ ተረካቢ ትውልድ ልታጣ ትችላለች::ልጆችና ታዳጊ ወጣቶች ላይ ብዙ ሊደከምባቸው ይገባል::የልጆች አገልግሎት ለተወሰኑ ሰዎች ተጥሎ ባወጣ ያውጣው ሊባል አይገባም::የቤ/ክርስቲያን ሙሉ ጊዜ አገልጋዮችና መሪዎች ትኩረት ሊሰጡት ይገባል::ስንት አብያተክርስቲያናት ናቸው ለልጆችና ለታዳጊ ወጣቶች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የመደቡት?ይህ ጥያቄ ሲነሳ የበጀት ጉዳይ ሊነሳ ይችል ይሆናል፤ሆኖም ግን ከልብ ካለቀሱ እንዲሉ የገንዘብ ችግር ብቻ ሳይሆን የእይታም ችግር ነው ያለብን::
አንዱ ችግር በአሁኑ ወቅት የሙሉ ጊዜ አገልጋይና የቤ/ክርስቲያን መሪ የሆኑ ሰዎች በአብዛኛው ስለ ልጆች አገልግሎት ተገቢ የሆነ ግንዛቤ የሌላቸው መሆኑ ነው::የተለምዶ አሠራር ከመከተል ውጪ ታስቦበትና ተጨንቆ የልጆችን አገልግሎት ማካሄድ ከእይታቸው ውጪ መሆኑን ማየት አይቸግርም::ይህን ችግር ለመቅረፍ ለመሪዎችና ለሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ጉዳዩ ያገባናል በሚሉ ወገኖች አግባብነት ያለው ሥልጠና ሊሠጥ ይገባል::ያን ጊዜ ስለ ልጆች አገልግሎት የመሪዎች ዓይን ይከፈታል::በልጆች ውስጥ ትውልድን ማየት ይችላሉ::ሕጻናትን ሳይሆን ትውልድን አሻግረው ማየት ይችላሉ::
የልጅነት ጊዜ በሰው ሕይወት ውስጥ ዋና ዋና የሆኑ ነገሮች የሚቀረጹበት ወቅት በመሆኑ ወሳኝ ነው::አንድ ጥናት እንዳመለከተው 75% የሆኑት የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በልጅነታቸው በሰንበት ት/ቤት በእግዚአብሔር ቃል ተኮትኩተው ያደጉ ናቸው:: በልጅነት ጊዜ የሚዘራ መልካም ዘር ለኋለኛው የሕይወት ዘመን እጅግ ጠቃሚ መሠረት እንደሆነ የእግዚአብሔር ቃልም ሆነ የስነ ልቦና አስተምሮ ይነግረናል::"ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም" (ምሳሌ22:6):: የስነ ልቦና ምሁራን የተናገሩትን ጠቅሶ አንድ ሰው እንዲህ ብሏል፥"አንድን ልጅ በተገቢ ሁኔታ የመጀመሪያውን 9 ዓመታት ካሳደግከው፥ከ11 እስከ 20 ዓመት ያለውን የዕድሜ ዘመኑን ትታደጋለህ፤ከ11-20 ያለውን የዕድሜ ዘመኑን በሚገባ ኮትኩተህ ከያዝከው ደግሞ ከ21-90 ዓመት ባለው የሕይወት ዘመኑ መልካም ሕይወት እንዲመራ ትረዳዋለህ::" (90 ዓመት ለመኖር ከታደለ ማለት ነው)
መልካም ነገሮችን የመዝሪያው ዕድሜ የአዋቂነት የዕድሜ ክልል አይደለም፤አዋቂዎችን ለመለወጥ እጅግ ይቸግራል(አይቻልም ባይባልም)::ልጆች ግን ምንም ነገር እንዳልተጻፈበት ነጭ ወረቀት የሆነ አእምሮ ስላላቸው የፈለግነውን ሁሉ በማስተማር በቀላሉ በጎ ተጽዕኖ ልናመጣባቸው እንችላለን (መጥፎ ተጽዕኖ ለማምጣትም አመቺው ጊዜ የልጅነት ወቅት መሆኑን ሳንዘነጋ)::
ቤ/ክርስቲያን የልጅነት ዕድሜ መልካም ዘር ለመዝራት ተገቢው ወቅት መሆኑን አውቃ ለአዋቂዎች የምትሰጠውን ያህል ትኩረት ለልጆች በመስጠት ልጆችን በመልካም መሠረት ላይ ልታንጽ ይገባል::ትኩረት መስጠት ስንል በደፈናው አይደለም::የሚለካ ሊሆን ይገባል::ይህም ማለት ከበጀቷ ስንት ስንተኛው ነው በልጆችና በልጆች ተዛምዶ ባለው ነገር ላይ የዋለው?የልጆች የመነቃቂያ ጊዜ ወይም ኮንፍራንስ አቅዳለች? የልጆች ሪትሪት ጊዜ አላት?ለልጆች አገልግሎት የሙሉ ጊዜ አገልጋይ መድባለች?እነደዚህ ዓይነት ፕሮግራሞችን አቅዶ ለማሳካት ማሰብን፥መነቃነቅን፥ድካምን፥ ብርቱ ጥረትንና የማያቋርጥ ክትትልን ይጠይቃል::የልጆች አገልግሎት እገሌ ይስራው ተብሎ የሚወረወር ጉዳይ አይደለም::የቤ/ክርስቲያን መሪዎች በአዋቂዎች የተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ እንደምንረባረበው ሁሉ ለልጆችም አገልግሎት እኩል ትኩረት ልንቸር ይገባል::ከዚህ አቅጣጫ የአመለካከት ለውጥ ልናመጣ ይገባል::ታዋቂው ሳይንቲስት አልበርት አይንስታን እንዲህ ብሏል፥" አንድን ነገር በተለመደው መንገድ እየሠራህ የተለየ ውጤት የምትጠብቅ ከሆነ አብደሀል ማለት ነው::" በተመሳሳይና በተለመደው መንገድ የልጆችን አገልግሎት እየመራን ለውጥ እናመጣለን ማለት ዘበት ነው::
በልጆች አገልግሎት የተሳካላቸው አብያተክርስቲያናት ካሉም ተመክሯቸውን መቅሰም ይገባል::የልምድ ልውውጥ ጊዜ በማዘጋጀት መማማር ይቻላል::በአዲስ አበባ የት/ት ቢሮ አማካኝነት በተቀናጀ መርሐ ግብር በግል ት/ቤቶች መካከል እየተካሄዱ ያሉ የልምድ ልውውጥ ጊዚያት ለየት/ት ቤቶቹ ያስገኙት ፋይዳ እጅግ ጠቃሚ መሆኑኑ በዝግጅቶቹ ላይ የተሳተፉ የት/ት ባለሙያዎች ያውቁታል::አብያተክርስቲያናትም የልጆችን አገልግሎት በተመለከተ የልምድ ልውውጥ መርሐ ግብር ቢያዘጋጁ ጠቀሜታው እጅግ የጎላ ነው::በተጨማሪም ጉዳዩ ያገባናል በሚሉ ወገኖች የምክክር ጊዜ(Panel Discussion) ቢዘጋጅ ብዙ ትምህርት ሊቀሰምበት እንደሚችል እምነት አለኝ::በልጆች አገልግሎት አቅጣጫ በእኔ እይታ ፈር ቀዳጅና ስኬታማ ሥራ በኢትዮጵያ እየሠራ የሚገኘው በወንድም ኤፍሬም የሚመራው ሻረን የልጆች አገልግሎት ለብዙዎች አብያተክርስቲያናት ግንዛቤ በማስጨበጥ ትልቅ ሚና መጫወት እንደሚችል እምነቴ ነው::
በርግጥ የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ ለልጆች የተስተካከለ መንፈሳዊ እድገት ኃላፊነቱ የቤ/ክርስቲያን ብቻ ነው የሚል እሳቤ የለውም::ወላጆች የበለጠ ኃላፊነት አለባቸው::ሆኖም ግን ቤ/ክርስቲያን የአገልግሎት ኃላፊነቷን ለመወጣት ስትንቀሳቀስ ለአዋቂዎች የምትሰጠውን ያህል ትኩረት ለልጆችም አገልግሎት ልትነፍግ አይገባም::ለልጆች የምንሰጠው አገልግሎት ምን ይመስላል?ልንፈትሽ ይገባል::የዛሬው ልጆች የነገ ታዳጊ ወጣቶች ናቸው፤የዛሬ ታዳጊ ወጣቶች የነገው ወጣቶች ናቸው::የዛሬው ወጣቶች የነገው የቤ/ክርስቲያን መሪዎች ናቸው::በርግጥ ብስለት ያላቸው አንዳንድ ወጣቶች ዛሬም የቤ/ክርስቲያን መሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ፤የሆኑም አሉ::ጢሞቴዎስ ወጣት የቤ/ክርቲያን መሪ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስን ዋቢ አድርገን መጥቀስ እንችላለን::
የልጆችን አገልግሎት ጠቄሜታን በተመለከተ ከwww. Ministry.To-Children.com ከተሰኘ ድዕረ ገጽ ላይ በመውሰድ ወደ አማርኛ የመለስኩትን ጠቃሚ ነጥቦች ከዚህ በታች በማስነበብ ጹሁፌን እደመድማለሁ::
የልጆች አገልግሎት ጠቀሜታው
ሀ. ለልጆች ያለው ጠቀሜታ
እግዚአብሔር ስለ ልጆች ይገደዋል፤እኛም ስለነሱ ሊገደን ይገባል::ልጆችን በእግዚአብሔር ቃል እውነት ስናገለግላቸው ብዙ የሚያገኙት ነገር አለ::ስምንቱ ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል::
1. ክርስቶስን እንደ ግል አዳኛቸው አድርገው ለመቀበል ይረዳቸዋል::
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ከማንኛውም የዕድሜ ክልል ይልቅ የልጅነት ወቅት ክርስቶስን ለመቀበል የተከፈተ ልብ የሚገኝበት ወቅት ነው:: በሌላ አነጋገር ልጆች ከአዋቂዎች ይልቅ ለጌታ ቅርብ ልብ አላቸው::ዕድሜያቸው እየጨመረ ሲሄድ ልባቸው እየጠነከረ ሊሄድ ይችላል::በመሆኑም በልጅነት ስለ ጌታ ኢየሱስ አዳኝነት መማራቸው ለመዳናቸው መንገድን ይከፍታል::
2. የሕይወት ትርጉም እንዲገባቸው ያደርጋል::
ግኡዙን አለም ማን እንደፈጠረው ማወቃቸው፥የሰውን ውድቀትና እግዚአብሔር የማዳንን መንገድ ማዘጋጀቱን መገንዘባቸው ለሕይወታቸው ትርጉም ይሰጠዋል::ለምን እንደሚኖሩ ከታናሽነታቸው ጀምሮ ይገባቸዋል::ለምን እንደሚኖር የገባው ሰው ትርጉም ያለው ሕይወት ይመራል::
3. ዘለቄታዊ ደስታን እንዲያጎለብቱ ይረዳቸዋል::
እግዚአብሔርን በማምለክ የሚገኘውን እውነተኛ ደስታ እንዲለማመዱ ይረዳቸዋል::በጌታ ደስ መሰኘትን ይማራሉ::እግዚአብሔር የእውነተኛ ደስታ ምንጭ ነውና::
4. አላስፈላጊ ከሆኑ አንዳንድ የኃጢአት አስከፊ ውጤቶች እንዲጠበቁ ይረዳቸዋል::
በርግጥ የእግዚአብሔር ፀጋ ብቻ ነው ልባችንን መቀየር የሚችለው::ሆኖም ግን እግዚአብሔርን አለመታዘዝ የሚያስከትለውን አስከፊ ጣጣ በልጅነት ማወቃቸው ልጆችን ጠንቃቃ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል::ኢየሱስ ሊያድናቸው የከፈለውን ትልቅ ዋጋ ሲረዱ፥በጽድቅ መንገድ ለመጓዝ ልባቸውን ያቀናሉ::የእግዚአብሔርን ጽድቅና ፍቅር ስናሳያቸው በፍቅሩ ልባቸው ሲማረክ፥ጽድቁንና ቅድስናውን ሲያውቁ ደግሞ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸው ልጆች ሆነው ያድጋሉ::በአክብሮትም ይገዙለታል::
5. የአለማዊነትን በጎ ያልሆነ ተጽዕኖ ለመቋቋም ይረዳቸዋል::
ሁላችንም በማህበረሰባችን ውስጥ ያለውን ክፉ ተፅዕኖ እናውቃለን::ይህን በጎ ያልሆነ ተፅዕኖ መቋቋም እንዲችሉ በጎና አዎንታዊ ተፅዕኖ የሚያመጣባቸው አካል ያስፈልጋቸዋል::ያም አካል የወላጆችና የቤ/ክርስቲያን ጥምር አስተዋፆ ነው::
6. ሌሎችን መውደድን ይማራሉ::
ሁለተኛው ታላቁ ትዕዛዝ "ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ" የሚለው ነው::ይህን ደግሞ በልጆቻችን ላይ ልናሰርጽ የምንችለው ለተቸገሩት ስንጸልይና ስንረዳ ሲያዩ ነው::ርህራሄ ተሞልተው እንዲያድጉ የሚታይ የፍቅር ሥራ እንደ ወላጅም እንደ ቤ/ክርስቲያን ልናሳያቸው ይገባል::
7. ጥሩ ጓደኞችን የሚያገኙበት ሥፍራ ይሆናል::
ልጆች ጥሩ ጓደኛ ከሚያገኙበት ሥፍራ አንዱ ቤ/ክርስቲያን ነው::
8. ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚተዋወቁበትና ዝማሬን የሚማሩበት ሥፍራ ይሆናል::
የቃል ጥቅሶችን እንዲያጠኑ ሲደረግ በአእምሮአቸው ስለሚሰርጽ በጎ ተጽዕኖ ያመጣባቸዋል::የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክንም እንዲማሩ ይረዳቸዋል::ዝማሬዎችንም በመስማትና በመዘመር እንዲያድጉ ያደርጋቸዋል::
ቤ/ክርስቲያን በዛሬው ተግባሯና በወደፊቱ ውጥኗ ለልጆችና ለታዳጊ ወጣቶች አገልግሎት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ወደ አዋቂዎች ያዘመመው አገልግሎቷ ሚዛናዊ ይሁን እላላሁ::አዋቂዎችንም ችላ እንበል የሚል እንድምታም የለኝም::ሁለቱንም እኩል እናገልግል::ያን ጊዜ ነው አገልግሎታችን ሙሉ የሚሆነው:: ጌታ ሁላችንንም ይባርክ!


Saturday, February 23, 2013


ውጤታማ ጸሎት
‹‹እግዚአብሔር በከንቱ ፈልጉኝ አላልኩም›› (ኢሳይያስ 45፡19) ብሏል፡፡ በምንጸልይበት ጊዜ በከንቱ አይደለም የምንጮኸው፤ ጊዜያችንን በከንቱ አይደለም የምናጠፋው፡፡ ይልቁን ጸሎትን ወደ ሚሰማና ወደ ሚመልስ አምላክ ነው የምንጸልየው፡፡ ምን ዓይነት ጸሎት ነው ውጤታማ የሚሆነው?ከዚህ በታች ጸሎትን ውጤታም የሚያደርጉ ስምንት ነጥቦችን እናያለን::  
1.  በቅን ልብ የሚጸለይ ጸሎት ውጤታማ ነው፡፡
በንጹሕ ልብ የሚጸለይ ጸሎት ኃይል አለው፡፡ ‹‹ቅንነት ግን ፊቱን ታየዋለች›› (መዝሙር 11፤7) ይላል ቃሉ፡፡ እግዚአብሔር በባሕሪው ቅን አምላክ ነው፤ ቅን የሆነው እርሱ ጸሎታቸውን በመመለስ የቅኖችን መንገድ ያቀናል (ዘዳ 32፤4 ኢሳ 26፤7)፡፡ ዳዊት ቅን ሰው ነበር፤ ጸሎቱም የሚሰማለት ሰው ነበር፡፡ ‹‹አቤቱ የኢኮጦፌልን ምክር ስንፍና አድርገህ እንድትለውጠው እለምንሃለሁ›› ብሎ ጸለየ (2ኛ ሳሙ 15፤31)፡፡ እግዚአብሔርም ጸሎቱን እንደመለሰለት መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ ‹‹እግዚአብሔርም በአሴሰሎም ላይ ክፉ ያመጣ ዘንድ እግዚአብሔር መልካሚቱን የኢኮጤፌል ምክር እንዲበትን አዘዘ›› (2ኛ ሳሙ 17፤14)፡፡ ዳዊት ለጠላቱ ለሳኦል የነበረው አመለካከት በቅንነት የተሞላ ነበር፤ የሳኦል ሞት በተነገረው ጊዜ ‹‹እስራኤል ሆይ ክብርህ በኮረብቶች ላይ ተወግቶ ሞቶአል›› (2ኛ ሳሙ 1፤19) በማለት ሳኦልን ‹‹የእስራኤል ክብር›› እያለ ያቆላምጠዋል፡፡  ስለ ሳኦልና ዮናታን ሲናገር ደግሞ ‹‹ከንሥርም ይልቅ ፈጣኖች፣ ከአንበሳም ይልቅ ብርቱዎች ነበሩ›› ብሏል (2ኛ ሳሙ 1፤23)፡፡
ስለ ሰዎች ያለን አመለካከት በቅንነት የተሞላ ሊሆን ይገባል፡፡ ጠማማ አስተሳሰብ ሊኖረን አይገባም፡፡ ሌሎች ሰዎች መልካም ነገር ሲሆንላቸው ልንደሰት፤ ችግር ሲገጥማቸው ደግሞ የሚያዝን ልብ ሊኖረን ይገባል፤ ያን ጊዜ ጸሎታችን የሚሰማልን ሰዎች እንሆናለን፡፡ ‹‹እርሱ ለቅኖች ደኅንነትን ያከማቻል፤ ያለ ነውር ለሚሄዱትም ጋሻ ነው›› (ምሳሌ 2፤7)፡፡ ‹‹ጠማማው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ርኩስ ነው፡፡ ወዳጅነቱ ግን ከቅኖችጋር ነው›› (ምሳሌ 3፤32) ይላል ቃሉ፡፡   
2.  እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ጸሎት ውጤታማ ነው፡፡
‹‹እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል›› (1ኛ ዮሐንስ 5፡14) ይላል የእግዚአብሔር ቃል፡፡ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ የእግዚአብሔርን ቃል ልናነብና ልንሰማ ይገባል፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ተገልጾአል፡፡ የጌታን ፈቃድ ለተለያዩ የግል ጉዳዮቻችን ለማወቅ ስንሻ ነገሮቹን አስመልክቶ የጌታ ሰላም በጉዳዩ ላይ መኖሩን ማረጋገጥ አለብን፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ በሆነ ጉዳይ ላይ ልባችን በእግዚአብሔር ሰላም ይሞላል፡፡ ጭንቀት የሚሰማን ከሆነ፥ጥድፍድፍ የሚያደርግ ውክቢያና ነውጥ የበዛበት ከሆነ ልናደርግ ባሰብነው ነገር ላይ ጊዜ ወስደን መጸለይ አለብን፡፡ የጌታን ፍጹም ፈቃድ እንድናገኝ  በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ የጸሎት ጊዜ ልንወስድ ይገባል፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ ዘለቄታዊ ጥቅማችንን የሚፈልግ ነው፡፡ ‹‹ለእናንተ የማስባትን ሀሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም›› (ኤር 29፡11)፡፡ እንዲሁም የእግዚአብሔር ቃል ‹‹ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች ፤ ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው›› (ምሳሌ 14፤12) ይላል፡፡ እግዚአብሔር ብቻ ነው የነገሮችን ፍጻሜ በውል የሚያውቀው፤ ባይገባንም እንኳ የእርሱን ምክርና ፈቃድ መቀበል መልካም ነው፡፡ ስለዚህ እርግጠኛ ባልሆንበት ጉዳይ ላይ ስንጸልይ ፈቃድህ ከሆነ ይሁን ፤ ፈቃድህ ካልሆነ ግን ይቅር እንበል፡፡  
3.  ትኩረትን በችግሮቻችን ላይ ሳይሆን በእግዚአብሔር ማንነት ላይ በማድረግ መጸለይ ውጤታማ ነው፡፡
ስለ ችግሮቻችን ብቻ የምናስብ ከሆነ እምነት እናጣለን፤፡ ያለ እምነት የሚጸለይ ጸሎት ደግሞ ውጤታማ አይሆንም፡፡  ቃሉ ‹‹በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በንፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባህር ማዕበል ይመስላልና፤ ሁለት ሃሳብ ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች የሚያገኝ አይምሰለው›› (ያዕቆብ1፡6-8) ይላል፡፡ ኢያሱ ለስለላ ከላካቸው መካከል አስሩ የተግዳሮቱን ብዛት አግዝፈው በማየታቸው ምድሪቱን እግዚአብሔር ሊያወርሳቸው እንደሚችል እምነት አጡ፤ ችግሮቻቸውን በእግዚአብሔር ዓይን ማየት ሲገባቸው እግዚአብሔርን በችግሮቻቸው ዓይን አዩት፤ ኢያሱና ካሌብ ግን ችግሮቻቸውንና ተግዳሮቱን በእግዚአብሔር ዓይን ሲያዩት  እንደ እንጀራ ሆኖ ታያቸው፡፡ እምነትም አገኙ፡፡ እንዲህ በማለትም ተናገሩ ‹‹…እንደ እንጀራ ይሆኑልናልና፣ የምድሪቱን ሰዎች አትፍሩ፤ ጥላቸው ከላያቸው ተገፎአልና፤ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው አትፍሯቸው›› ዘኁልቁ (14፤9)፡፡ በተጨማሪም ካሌብ ‹‹ማሸነፍ እንችላለንና እንውጣ እንውረሰው›› (ዘኅልቁ 13፤30) በማለት እምነቱን ገለጸ፡፡ አስሩ ሰላዮች ባመጡት ወሬ ውስጥ የጠላትን ትልቅነትና ግዝፈት አጉልተው ሲናገሩ አንዴ እንኳን የእግዚአብሔርን ስም በአዎንታዊ መልኩ አልጠቀሱትም፡፡ ኢያሱና ካሌብ ግን ሦስት ጊዜ የእግዚአብሔርን ስም ጠቅሰው ተናግረዋል (ዘኅልቁ 13:26-33፤14:7-9)፡፡ ስለዚህ በምንጸልይበት ገዜ የእግዚአብሔርን ታላቅነትና ሁሉን ቻይነት እያሰብን ሊሆን ይገባል፡፡
ጆርጅ ሙለር የተባለው የ19ኛው ክፍለ ዘመን የእምነት ሐዋሪያ በአንድ ወቅት ወደ ካናዳ ለአገልግሎት በመርከብ ይጓዝ ነበር፡፡ በባህር ላይ ሲጓዙ መንገዳቸው በጭጋግ ስለ ተሸፈነ መርከቡ መጓዝ ተስኖት ነበር፡፡ ጆርጅ ሙለር ካናዳ አገልግሎት ስለ ነበረው ሁኔታው አልተመቸውም፡፡ ወደ መርከብ ነጂው ሄዶ በፍጥነት እንዲያደርሰው ጠየቀው፤ የመርከቡም ነጂ ‹‹ይህ ሰው ጤነኛ ነው?›› በማለት ካሰበ በኋላ ከፊታቸው የተደቀነውን ጭጋግ በጣቱ እየጠቆመ ‹‹አይታይህም እንዴ? መሄድ እንችላለን በዚህ ሁኔታ?›› አለው፡፡ ጆርጅ ሙለር የተደቀነውን ጭጋግ ሳያይ ‹‹የሕይወቴን የእያንዳንዱን ሁኔታ የሚቆጣጠረውን አምላኬን ነው የማየው፤ አንተ ልትረዳኝ ካልቻልክ ሌላ የሚረዳኝ አለ›› ብሎ ወደ መርከቡ የታችኛው ክፍል ለጸሎት ወረደ፡፡ የመርከቡ ነጂም ክርስቲያን ስለነበረ ይሉኝታ ተሰምቶት ለመጸለይ ጆርጅ ሙለርን ተከትሎ ሄደ፡፡ ጆርጅ ሙለር አጭር ጸሎት ጸለየና ከጸሎቱ በመነሳት ሊጸልይ የነበረውን የመርከቡን ነጂ እንዲህ አለው፤ ‹‹አየህ፣ አንተ መጸለይ አያስፈልግህም፤ በመጀመሪያ ደረጃ አንተ እምነት የለህም፤ ሁለተኛ ደግሞ እኔ ስለ ጸለይኩ አንተ መጸለይ አያስፈልግህም፡፡ አየህ ካፒቴን፣ ከጌታ ጋር ላለፉት አምሳ ሰባት ዓመታት ስኖር አንድም ቀን አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ሂድ ወጥተህ እይ አለው›› መርከብ ነጂው ወጥቶ ሲያይ ጉሙ ተብትኗል፤ ሕይወቱ በዚህ የአምነት ተዓምር በጣም ተነቃቃ፤ ጆርጅ ሙለርም ባሰበው ሰዓት ለአገልግሎት ካናዳ ደረሰ፡፡ በእግዚአብሔር እመኑ፡፡ ‹‹እውነት እውነት እችኋለሁ፤ ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር ይህን ተራራ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል፤ ስለዚህ እላችኋለሁ፤የጸለያችሁትን የለመናችሁትን ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፣ ይሆንላችሁማል›› (ማርቆስ 11፡23-24)፡፡  
4.  ጌታን በመታዘዝ የሚደረግ ጸሎት ውጤታማ ነው፡፡
የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል፡- ‹‹በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆናላችሁማል›› (ዮሐንስ 15፤7)፡፡ በተጨማሪም እንዲህ ይላል፡- ‹‹ትዕዛዙንም የምንጠብቅና በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን የምናደርግ ስለሆንን የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እናገኛለን››(1ኛ ዮሐንስ 3-22)፡፡   ከእነዚህ ጥቅሶች ጌታን መታዘዝ ለጸሎታችን መመለስ ወሳኝ መሆኑን ልንገነዘብ እንችላለን፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል እንታዘዝ፤ እግዚአብሔርም ጸሎታችንን ይሰማል፡፡ ዓመጸኞች ከሆንን ግን ጸሎታችንን አይሰማም፡፡ አለመታዘዝ በደል ነው፤ በደል ደግሞ ጸሎት እንዳይመለስ እንቅፋት ይሆናል፡፡ ‹‹እነሆ የእግዚአብሔር እጅ ከማዳን አላጠረችም፤ ጆሮውም ከመስማት አልደነቆረችም፡፡ ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና አምላካችሁ መካከል ለይታለች፤ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል›› (ኢሳይያስ 54፤1-2)፡፡ ስለዚህ ራሳችንን በጸሎት በጌታ ፊት በመፈተሸ ያልታዘዝነው ነገር ካለ በመናዘዝ ንስሐ እንግባ፤ ከዚያም ጌታ ጸሎታችንን ይሰማል፡፡  
5.  በኢየሱስ ስም የሚጸለይ ጸሎት ውጤታማ ነው፡፡
በራሳችን ስም ወደ እግዚአብሔር አብ የመቅረብ ብቃት የለንም፤ጽድቃችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በልጁ ስምና ደም በኩል ወደ አብ መግባት አግኝተናል፡፡ ‹‹እውነት እውነት  እላችኋለሁ፡- አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል›› (ዮሐ 16፤24)፡፡ ‹‹ማንኛውን ነገር በስሜ ብትለምኑት እኔ አደርገዋለሁ›› (ዮሐ 14፤14) ብሏል ጌታ ኢየሱስ፡፡ ሁል ጊዜ ወደ እግዚአብሔር አብ ስንቀርብ ጽድቃችን ክርስቶስ እንደሆነ ማወቅ አለብን፡- ‹‹ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብ፣ ጽድቅ፤ ቅድስናም፣ ቤዛነትም በተደረገልን በክርስቶስ ኢየሱስ የሆናችሁ ከእርሱ ነው›› (1ኛ ቆሮ 1፡31)፡፡  
6.  ሁለት ሆኖ በመስማማት የሚደረግ ጸሎት ውጤታማ ነው፡፡
‹‹ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማይ ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል›› (ማቴዎስ 18፤19)፡፡ የልብ አንድነት ትልቅ ሥራ ይሰራል፡፡ ስለዚህ ቢያንስ አንድ የልብ የሆነ የጸሎት ጓደኛ ያስፈልገናል፡፡ ልባችን የሚቀባበልና የማይገፋፋ የጸሎት ወዳጅ ያስፈልገናል፡፡ ሁለትና ሶስት ከተገኙ መታደል ነው፡፡ ቢያንስ ግን አንድ የጸሎት ወዳጅ ያስፈልገናል፡፡ በልብ አንድነት የማይጸለይ ጸሎት ከጣራ አያልፍም፤ ከንቱ ልፍለፋ ነው፡፡  
7.  ከልብ የሚደረግ ጸሎት ውጤታማ ነው፡፡
‹‹ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ስለ እርሱ (ጴጥሮስ) ወደ እግዚአብሔር ጸሎት አጥብቆ ይደረግ ነበር›› (ሐዋ 12፡5)፡፡ ‹‹አጥብቆ›› የሚለው ቃል በሙሉ ልብ የሚደረግ ጸሎት እንደነበር ያሳያል፡፡ እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ሰምቶ መልአኩን ላከ፤ ጴጥሮስንም ከእስር ቤት አስወጣው፤ከተቀጠረለትም ሞት አዳነው፡፡ ጴጥሮስን ወደ ጸሎቱ ስፍራ ላከው፡- ‹‹ባስተዋለም ጊዜ (ጴጥሮስ) እጅግ ሰዎች ተከማችተው ይጸልዩበት ወደ ነበረው ማርቆስ ወደ ተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት መጣ›› (ሐዋ 12፤12)፡፡ ስለዚህ ስንጸልይ ከልባችን ልንጸልይ ይገባል፤ በግማሽ ልብ የሚጸለይ ጸሎት ኃይል የለውም፡፡ በሙሉ ልባችን ልንጸልይ ይገባል፡፡  
8.  በጾም የሚጸለይ ጸሎት ውጤታማ ነው፡፡
በምንጾምበት ጊዜ ከምግብ ይልቅ ለጌታ ነገር ቅድሚያ መስጠታችንን ያሳያል፤ ጾም ራሳችንን ለማዋረድ ይረዳናል፡፡ ልባችንንም ለእግዚአብሔር ነገር ለማዘጋጀት በጣሚ ጠቃሚ ነው፡፡ በምንጾምበት ጊዜ መንፈሳችን ለመጸለይ የበለጠ ይዘጋጃል፡፡
የተለያዩ የጾም ዓይነቶች አሉ፡-
ሀ. የአጭር ጊዜ ጾም
         ቁርስን ብቻ መጾም (የ6 ሰዓት ጾም)
         ቁርስንና ምሳን መጾም (የ12 ሰዓት ጾም)
         ቁርስ፣ ምሳና እራት መጾም (የ24 ሰዓት ጾም)
         የ3 ቀን ጾም (ብዙ ውሃ መጠጣት አለብን፤ አካላችን ውሃ በማጣቱ የተነሳ የጤና ቀውስ ውስጥ እንዳንገባ)
ለ. የረጅም ጊዜ ጾም
     የ7 ቀን ጾም
     የ21 ቀን ጾም
     የ40 ቀን ጾም
ረዘም ላለ ጊዜ የምንወስደው ጾም (የ7 ቀን፣ የ21 ቀንና የ40 ቀን ጾም) በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ሊሆን ይገባል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ከሆነ የምንጾመው መንፈስ ቅዱስ ለሚሞተው ሰውነታችን ኃይልና ሕይወት ይሰጣል፡፡ በእነዚህ የጾም ቀናት ብዙ ፈሳሽ መውሰድ አለብን፡፡ ያለ መንፈስ ቅዱስ ምሪት ረዘም ያለ ጾም መጾም የለብንም፤ ያለ መንፈስ ቅዱስ ምሪት ረዘም ያለ ጾም መጾም ለአጋንንቱ ዓለም ሊያጋልጠን ይችላል፡፡ ከክርስቶስ እምነት ውጪ የሆኑ ኃይማኖቶችም ጾም እንደሚጾሙ ማስተዋል አለብን፡፡ ጾም በራሱ የሚፈይደው ነገር የለም፤ ከጌታ ጋር ያለን ግንኙነት  ወሳኝ ነው፡፡ ግልጽ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ማነሳሳትና ምሪት ካገኘን ረዘም ያለ የጾም ጊዜ መውሰድ ለብዙ ድል ያበቃናል፡፡ ቀንበር ይሰበርልናል፤ መለኮታዊ ምሪት እናገኛለን፤ የጠላት ሥራ ይፈርሳል፤ ጥሰት/ ጥርመሳ (breakthough) እናገኛለን፤ የ3 ቀን ፣ የ7 ቀን ፣ የ21 ቀን ፣የ40 ቀን ጾም ስንጾም ማታ ላይ ለስለስ ያሉ ምግቦችና ፈሳሽ በመውሰድም መጾም ይቻላል፡፡ በተለይ ያለ ምግብ ከሦስት ቀናት በላይ የምንቆይበት ጾም ከያዝን ስንፈስክ በጣም መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ ቀጠን ያሉ ፈሳሾችን በመውሰድ ቀስ በቀስ ወደ ጠንካራው ካልተሸጋገገርን ትልቅ የጤና ችግር ሊያስከትልብን ይችላል፡፡ የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች (ለምሳሌ እንደ ስኳር በሽታ ዓይነት) ረዘም ያለ ጾም ከመያዛቸው በፊት ሐኪም ቢያማክሩ መልካም ነው፡፡
በታሪክ ውስጥ የተነሱትን ታላላቅ የእግዚአብሔር ሰዎች ታሪክ ስናነብ በሳምንት አንድ ቀን በተለይ ዓርብ፣ ዓርብ የጾም ጸሎት ቀን እንደሚያደርጉት አግኝተናል፡፡ ስለዚህ ቢቻል በሳምንት አንድ ቀን በጌታ ፊት እራሳችንን የምናዋርድበት፣ ሕይወታችንን በቅዱስ ብርሃኑ የምናስፈትሽበት፣ የምንታደስበት፣ የአምላካችን ፊት የምንፈልግበት የጾም ቀን ቢኖረን መልካም ነው፡፡  
የሕይወት ቀንበር ሲከብድብን፥ጨለማ መንገዳችንን ሸፍኖት ምንም ተስፋ አልታይ ሲለን፥ሰፋ ያለ የጾም ጸሎት ጊዜ መውሰድ መልካም ነው፡፡ ቢቻል ጥሞና  ልናገኝ የምንችልበት ምቹ ቦታ ሄደን ሰብሰብ ባለ አእምሮ ብንጸልይ ብዙ በረከት ልንቀበል እንችላለን፡፡ ለሕይወታችን ጌታ አዲስ አቅጣጫ ይሰጠናል፤ በመንገዳችንም ላይ መለኮታዊው ብርሃኑን ስለሚፈነጥቅልን የከበበን ጨለማ ይበተናል፡፡ በመንፈሱም ይሞላናል፤የመታደስ ጊዜ ይሆንልናል፡፡
በየአብያተ ክርስቲያናቱ በሚታወጁት ጾም ጸሎቶች ላይ መሳተፍ ለሕይወት ልምላሜና ተሃድሶ እጅግ ጠቃሚ ነው፤ ከቅዱሳን ጋር ስንከማች የበለጠ ኃይል ይለቀቃል፡፡ የጌታ ዓላማ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ስለሆነ ለአካሉ በሚለቀቀው ኃይልና ቅባት እንሞላለን፡፡  
ስለ ጾም የተጠቀሱ ጥቅሶች
‹‹አሁንስ ይላል እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሁ በጾምም፣ በለቅሶ፣ በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ፤ ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር ቸርና መሓሪ፣ ቁጣው የዘገየ፣ ምሕረቱም የበዛ፣ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ›› (ኢዮኤል 2፡12-13)፡፡ በጽዮን መለከትን ንፉ፤ ጾምንም ቀድሱ፤ ጉባኤውንም አውጁ፤ ሕዝቡንም አከማቹ፤ማኅበሩንም ቀድሱ ሽማግሌዎችንም ሰብስቡ፤ ሕጻናቱንና ጡት የሚጠቡትን አከማቹ፤ ሙሽራው ከእልፍኙ፣ሙሽሪቱም ከጫጉላ ይውጡ›› (ኢዩኤል 2፡15-16)፡፡ ‹‹ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፡፡ በዚያን ወራት ይጦማሉ›› (ማርቆስ 2፤20) ‹‹ይህ ወገን በጸሎትና በጾም ካልሆነ በምንም ሊወጣ አይችልም አላቸው›› (ማርቆስ 9፤29)፡፡  ‹‹እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ በርናባስንና ሳውልን ለጠሯኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ›› (ሐዋ 13፤2)፡፡
ከምግብ ይልቅ የጌታን ፊት በመናፈቅ አስኪ ራሳችንን እናዋርድ፤ በመጾም ስንጸልይ የብዙዎች ቀንበር ይሰበራል፤ እስራት ይበጣጠሳል፤ ተሐድሶ ወደ ሕይወታችንና ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጣል፤ ብዙዎችም ከጨለማው መንግሥት ፈልሰው ወደ ጌታ መንግሥት ይመጣሉ፡፡
ወ/ም ተድላ ሲማ
                   

Monday, November 19, 2012



ተሐድሶ 

የነህምያ መጽሃፍን መሰረት ያደረገ ትምህርት

ተሐድሶ ማለት ሁኔታዎች እግዚአብሔር ወዳሰበው ወይም ወዳሰመረው መስመር ሲመጡ ማለት ነው:: በአሁኑ ጊዜ ያለችው ቤተ ክርስቲያን በሐዋሪያት ዘመን ከነበረችው ቤተ ክርስቲያን በእጅጉ የተለየች ሆናለች:: ይህም ከቅድስና፥ ከፍቅርና እግዚአብሔርን ከመፍራት አንጻር ሊታይ ይችላል:: እንደ ቤተ ክርስቲያን የት ነው ያለነው? እንደ ክርስቲያን ተሐድሶ አያስፈልገንም? ቤተ ክርስቲያን ያለነቀፋና ያለምንም ፊት መጨማደድ መሆኗ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው:: ተሐድሶ እንዲመጣ ምን ቅድመ ሁኔታ ሊሟላ ይገባል?  

ተሐድሶ እንዲመጣ ሦስት ቅድመ ሁኔታዎች

•         የነገሮች ወይም ሁኔታዎች መበላሸት ወይም የቀድሞ ሁኔታቸውን ማጣት

•         በሁኔታዎቹ መበላሸት የሚቆጭና የሚያዝን ሰው መኖር (ሸክም ያለው ሰው መኖር)

•         የተበላሸው ሁኔታ እንዲቀየር ርምጃ የሚወስድ ሰው መኖር (ዋጋ የሚከፍል ሰው መገኘት)  

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተሐድሶ ካመጡ ሰዎች አንዱ ነህምያ ነው::  የነህምያን መጽሐፍ ስንቃኝ ከላይ የተጠቀሱት ሶስት ሁኔታዎች ተሟልተው እናገኛለን::  

1-     በመጀመሪያ ደረጃ የኢየሩሳሌም የቀድሞ ሁኔታ ተበላሽቶ ነበር:: ቅጥሮቿ ፈርሰው፥ በሮቿ ተቃጥልው፥ ሕዝቧ ተማርከውና ከምርኮ የተረፉትም በታላቅ ጉስቁልና ውስጥ ነበሩ (ነህምያ 1:3):: በአጠቃላይ የህዝቡ ውጫዊ (Physical) እና መንፈሳዊ (Spiritual) ሁኔታ የተበላሸ ነበር::  

2-    በሁለተኛ ደረጃ ስንመለከት ሁኔታውን ሲያይ የተቆጨ፥ ያዘነና ትልቅ ሸክም የወደቀበት ሰው ነበር:: ያም ሰው ነህምያ ነበር:- "ይህንም ቃል በሰማሁ ጊዜ ተቀምጬ አለቀስሁ፥አያሌ ቀንም አዝን ነበር::በሰማይም አምላክ ፊት እጾምና እጸልይ ነበር" (ነህምያ 1:5-11)::  

3-   በመቀጠልም የተበላሸውን ሁኔታ ለማስተካከል እርምጃ የወሰደን ሰው እናገኛለን:- ነህምያ:: የመጀመሪያው ርምጃ በጌታ ፊት መጾምና መጸለይ ነበር:: ከዚያም እግዚአብሔር ሁኔታዎችን ሲያመቻችለት ለንጉሱ ጥያቄ አቀረበ:: በመቀጠልም የምቾት ቀጠናውን በመተው ወደ ኢየሩሳሌም የሚወስደውን ረጅም ጉዞ ተያያዘው:: ዋጋ ሳይከፈል ተሀድሶ አይመጣም:: የተሃድሶ ሰዎች ቁርጠኞች ናቸው:: ተሐድሶን በተመለከተ ሌላ የምናስተውለው ነገር ለተሀድሶ መነሳት አንድ ሰው በቂ መሆኑን ነው:: ይህ ሰው የነቃ፥ የተነቃቃና የሚያነቃቃ ሲሆን ሁኔታዎች መለወጥ ይጀምራሉ:: ነህምያ የተበላሸ ሁኔታ እንዳለ ሲያይ ይህ ልክ አይደለም ብሎ ነቃ:: በመቀጠልም በጾምና በጸሎትተነቃቃ:: በመጨረሻም ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ሕዝቡን አነቃቃ:: እንዲህ አላቸው:- "እኛ ያለንበትን ጉስቁልና፥ኢየሩሳሌም እንደ ፈረሰች፥ በሮቿም በእሳት እንደ ተቃጠሉ ታያላችሁ:: አሁንም ከእንግዲህ ወዲህ መሳለቂያ እንዳንሆን ኑና የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንሥራ" (ነህ 2:17):: ይህንን ሲሰሙ ሕዝቡ ተነቃቁ:- "እንነሣና እንሥራ" አሉ (ነህ 2:18)::

ተሐድሶና ተግዳሮቶች(Challenges)

ተሐድሶ ለማምጣት የሚንቀሳቀስ ሰው የተለያዩ ተግዳሮቶች ይገጥሙታል:: ነህምያም በእስራኤላውያን መካከል ተሐድሶ ለማምጣት ሲንቀሳቀስ የተለያዩ ተግዳሮቶች ገጥመውታል:: ለእያንዳንዱ ተግዳሮት ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ወደ ተሐድሶ ሊደርስ ችሏል:: ከዚህ በመቀጠል ነህምያ የገጠሙትን ስድስት ተግዳሮቶችና ለነዚህም ተግዳሮቶች የሠጠውን ምላሽ እናያለን::  

1-     ነህምያ ለተሐድሶ ሲንቀሳቀስ የገጠመው የመጀመሪያው ተግዳሮት የተቃዋሚዎች የንቀት ሳቅ ነበር:- "በንቀት ሳቁብን" (ነህ 2:19) ሲል ነህምያ ይገልጸዋል:: አላማውም ተሰፋ ለማስቆረጥ ነበር:: ለዚህ ነህምያ የሠጠው ምላሽ የእምነት ቃል መናገር ነበር:- " የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል:: እኛም ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን" (ነህ 2:20):: ለተሐድሶ ስንነሳ ሰይጣን ተስፋ ሊያስቆርጠን ይሞክራል:: እኛም እንደ ነህምያ የእምነት ቃል በመናገር ወደሚቀጥለው ሥራ መሸጋገር አለብን::  

2-    ይህ ባልተሳካ ጊዜ የነህምያ ጠላቶች በቁጣና በብስጭት በመነሳት በአይሁድ ላይ ማላገጥና መቀለድን ተያያዙ:-"በድንጋይ በሚሠሩት ቅጥራቸው ላይ ቀበሮ ቢመጣበት ያፈርሰዋል" የሚል ፌዝ አፌዙ (ነህ 4:3):: አሁንም አላማቸው ተስፋ በማስቆረጥ እና ልባቸውን በማድከም ከተሐድሶው ሥራ ለመግታት ነበር:: ነህምያ ለዚህ የሠጠው ምላሽ እየጸለየ ሥራውን ማቀላጠፍ ነበር (ነህ 4:5-6):: ከዚህም የተነሣ የቅጥሩ ሥራ በዚህ ሰዓት እስከ እኩሌታው ተጋጠመ (ነህ 4:6):: በተሐድሶ የተግባር ሂደት ውስጥ የሚገጥሙንን የጠላት ፌዝና ልብ አድካሚ ተገዳሮቶችን ለጌታ በጸሎት በመንገር ሥራችንን ማቀላጠፍ ነው ያለብን:: የትኩረት አቅጣችንን ለማግኘት ጠላት ደፋ ቀና ማለቱን አይተውም:: ሁልጊዜ በጸሎት መንፈስ ውስጥ ልንሆን ይገባል::

3-   ቀጣዩ የጠላት ስትራቴጂ እስራኤልን ለመውጋትና ለማሸበር መማማል ነበር (ነህ 4:8):: ይህንንም የጠላት ሤራ ለማክሸፍ እነ ነህምያ ያደረጉት የሚከተለውን ነው:- "ወደ አምላካችንም ጸለይን፥ከእነርሱም የተነሣ በአንጻራቸው ተጠባባቂዎች በሌሊትና በቀን አደረግን::...ከቅጥሩም በስተኋላ በኩል ባለው በታችኛው ስፍራ ሰይፋቸውን፥ጦራቸውንም ቀስታቸውንም አስይዤ ሕዝቡን በየወገናቸው አቆምኋቸው"( ነህ 4:9 13):: ለተሐድሶ የሚነሱ ሰዎች የጠላት ኢላማ መሆናቸው የማይቀር ነው:: በመሆኑም በጌታና በኃይሉ ችሎት በመበርታት ጠላትን በመዋጋት፥ዕቅዱንና አሳቡን ሊያፈርሱ ይገባል:: ምሽግን ለማፍረስ ብርቱ የሆኑ መንፈሳዊ የጦር ዕቃዎች አሉን:: የእግዚአብሔርን ቃል፥ እምነት፥ የኢየሱስን ስም፥ የህብረት ጸሎትና የደሙን ኅይል በመጠቀም የጠላትን ውጊያ ሁሉ ልናፈርስ ይገባል:: የምንዋጋው ከተሸነፈ ጠላት ጋር መሆኑን መዘንጋት የለብንም (ቆላስያስ 2:15፥ ዕብራውያን 2:14151 ጴጥሮ 3:22)::  

4-   ሌላው ነህምያ የገጠመው ተግዳሮት በእስራኤላውያን መሐከል የተነሣው የውስጥ ችግር ነበር:: የነበረባቸው የኢኮኖሚ ችግር የተጀመረውን ተሐድሶ ተፈታትኗል:: እስራኤላውያን የእስራኤላውያንን (የወገኖቻቸውን) የእርሻ መሬቶች በብድር ምክንያት ይዘው ነበር:: ሕዝቡ ተርቦ ነበር:: ይህ የውስጥ ችግር ከሌሎቹ ተግዳሮቶች ይልቅ ነህምያን አስቆጥቶት ነበር:: በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ወደ ተሐድሶ ስንገሰግስና በተሐድሶ ውስጥ ስንሆን የሚገጥመን ትልቁ ተግዳሮት ከውጪ የሚመጣው የጠላት ሠልፍ ወይም ውጊያ ሳይሆን በቅዱሳን መካከል የሚነሳው ጠብና ሹኩቻ ነው:: ነህምያ የገጠመውን ችግር በጥበብ ሊፈታው ችሏል:: እኛም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተሐድሶ ወቅት የሚገጥመንን ችግር በጠብ ሳይሆን በጥበብ ልንፈታው ይገባል:: በታሪክ ውስጥ ስናይ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተነሡ ተሐድሶዎች ሊገቱ የቻሉት በቅዱሳን መካከል በተነሱ አለመግባባቶች፥ ፀቦች፥ ሹኩቻዎችና ራስ ተኮር(Self Centered Life Style) አካሄዶች እንጂ ከውጪ በሆነ ውጊያ አለመሆኑን እንገነዘባለን:: እግዚአብሔርን ያላማከለ ሕይወትና የራስን ክብር መፈላላግ የመስቀሉ ጠላቶች በመሆን የጌታን ሥራ ያበላሻሉ:: ለዚህ መፍትሄው ራስን መካድና ለጌታ ደስታ መኖር ነው::  

5-   በተሐድሶ ግስገሳ ውስጥ ሌላው ነህምያን የገጠመው ተግዳሮት ሽንገላ ነው:: ጠላቶቹ ከዚህ በፊት የሞከሩት አፍራሽ ስልት ሁሉ እንዳልተሳካና የማደሱ ሥራ ሳይገታ መቀጠሉን ሲያዩ ሌላ ዘዴ ይዘው መጡ:-ሽንገላ:: ለርሱ የተቆረቆሩ በመምሰል ነህምያን ለምክክር ስብሰባ አምስት ጊዜ ጠሩት:- "እንግዲህ መጥተህ በአንድነት እንማከር"የሚል ጥሪ ነበር (ነህ 6:2-9):: ለዚህም ሽንገላ ነህምያ የሠጠው ምላሽ "ትልቅ ሥራ እሠራለሁ፥ እወርድም ዘንድ አይቻለኝም" የሚል ነበር:: ጠላት ሁልጊዜ የሚፈልገው የጀመርነውን የተሐድሶ ሥራ አቋርጠን ከከፍታችን እንድንወርድ ነው:: በተሐድሶ ሥራ ውስጥ ያለ ሰው ለጠላት ሽንገላ አግባባዊ መልስ ሊሠጥ ይገባል እንጂ የትኩረት አቅጣጫውን ሊስት አይገባም::  

6-   የመጨረሻው የጠላት ሙከራ ሐሰተኛ ነብይ በመላክ ነህምያን ለማሳሳት መሞከር ነበር:: ነህምያ ማድረግ የማይገባውን ነገር እንዲያደርግና በደል እንዲፈጽም ለማሳሳት ነበር(ነህ 6:10-14):: ሆኖም ነህምያ የጠላቶቹን ሤራ በማስተዋል ከስህተት ሊጠበቅ ችሏል:: የዲያቢሎስን ሽንገላ እንድንቃወም የእግዚአብሔር ቃል ያሳስበናል (ኤፌሶን 6:11):: ዓለምን ያሳተው የቀደመው እባብና ዘንዶ (ሰይጣን ወይም ዲያቢሎስ) ዋናው ሥራ በመሸንገል ማሳት ነው:: በእግዚአብሔር ቃልና በጥበብ በመሞላት ሤራውን ልናስተውል ይገባል:: "በሰይጣን እንዳንታለል የእርሱን አሳብ አንስተውምና" ይላል ቃሉ (2 ቆሮ.2:11)::  

እነዚህን ሁሉ ተግዳሮቶች በድል ከተወጣ በኋላ ነህምያ ለተሐድሶ መምጣት ምክንያት መሆን ችሏል:: እልህ አስጨራሽ የነበረውን ውጣ ውረድና ፈተና ካለፉ በኋላ እነ ነህምያ የሚከተለውን ውጤት ለማየት በቅተዋል:-

በነህምያ መጽሃፍ የተጠቀሱ የተሐድሶ ውጤቶች

1. ቅጥሩን የማደስ ሥራ 52 ቀናት ማጠናቀቅ ችለዋል( ነህ 6:15)  
2. ጠላቶቻቸውን ሁሉ ማሳፈር ችለዋል (ነህ 6:16)  
3. ከዚህም የተነሳ መንፈሳዊ ተሐድሶ ሊመጣ ችሏል:- እስራኤላዊያን ሁሉ በእግዚአብኤር ፊት ኃጢአታቸውንና የአባቶቻቸውን ኃጢአት ተናዘዋል (ነህ 9:3)  
4. ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ቃል ሊሰሙ ችለዋል (ነህ 9:3)  
5. ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ሰገዱ (ነህምያ 9:3)  
6. በሕዝቡ መሐከል እጅግ ታላቅ ደስታ ሆነ (ነህ 8:17)  
7. ሕዝቡም ተቀደሱ (ነህ 9:2)  

መደምደሚያ

የተሐድሶ ግብ ቅዱሳን ኃጢአታቸውን በመናዘዝና በመተው በመንፈስና በእውነት እግዚአብሔርን ወደ ማምለክ ሲመጡ ነው:: እግዚአብሔርን በመፍራት መቀደስ ሲችሉ እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል በክብሩ ይመላለሳል:: እግዚአብሔርም ይከብራል:: የመኖራችን ግብ እግዚአብሔርን ማስከበር ከሆነ በተሐድሶ ሕይወት ውስጥ መሆናችንን ልንገነዘብ ይገባል:: በተቃራኒው ሁሉጊዜ ስለራሳችን ጥቅም፥ክብር እና ዝና የምናስብና በሥጋዊ ምኞት የተዋጥን ከሆነ ተሐድሶ ያስፈልገናል:: ለተፈጠርንለት አላማ እየኖርን አይደለም:: ጌታ ሆይ በተሀድሶ ጎብኘን ብለን ልንጸልይ ይገባል:: እግዚአብሔር ያየልንን ሕይወት ኖረን እንድናልፍ ጌታ ይርዳን:: ጥሪያችን እንደ ንስር እንድንኖር እንጂ እንደ ዶሮ ምድር ምድር እያየን ምድራዊ ሆነን እንድንቀር አይደለም:: ተሐድሶ ቤተክርስቲያን ጌታን የምትወድ፥ያለ ነቀፋና ያለ ምንም ፊት መጨማደድ የሆነች እንድትሆን ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል::
 

በወንድም ተድላ ሲማ