አዋቂ ተኮር አገልግሎት ቢቀየርስ
በወ/ም ተድላ ሲማ
ሐዋሳ ከተማ ውስጥ በልጆች አገልግሎት ላይ ሸክም የነበረው
አንድ ወንድም እንዲህ አለ፥"አይ ቤ/ክርስቲያን፥ ለሙን መሬት ትታ በጭንጫ ላይ ዘር በመዝራት ትደክማለች::" ይህ
ሰው ይህን ያለው የአንዲት አጥቢያ ቤ/ክርስቲያን ምዕመናን ቤ/ክርስቲያን ውስጥ ተቀምጠው መንፈሳዊ ፕሮግራም ሲካፈሉ፥ ልጆቹ
ግን ውጪ ፀሐይ ላይ ሲንቃቁ በማየቱ፥ለምን ትኩረት ተነፈጋቸው? በማለት ነበር::በርግጥ አዋቂዎችን በ"ጭንጫ" መመሰሉ
ጠንከር ያለ አባባል ሊመስል ይችላል::ለአዋቂዎች የሚሰጠው ትኩረት ተገቢ አይደለም ለማለት አይደለም የዚህ ጽሑፍ ዓላማ፤ሆኖም
ግን በቤ/ክርስቲያን ውስጥ የሚታቀዱት ፕሮግራሞች በአብዛኛው አዋቂ ተኮር መሆናቸውን ለማሳየትና ይህ አካሄድ እንዲስተካከል
ለማስገንዘብ ነው::ከቤ/ክርስቲያን በጀት አብዛኛው አዋቂ ተኮር ለሆኑ ዕቅዶች እንጂ ልጆችን ያማከለ እንዳልሆነ የአደባባይ
ሚስጥር ነው:: ለመሆኑ የልጆች ኮንፍራንስ የሚል ሰምተን እናውቃለን? አብዛኛው የቤ/ክርስቲያን አገልጋዮች ጊዜና ጉልበት
የሚባክነው አዋቂዎችን በማገልገል ነው ወይስ ልጆችን?የልጆች ቁጥር በአንዳንድ አብያተክርስቲያናት ከአዋቂው የማይተናነስ መሆኑም
መዘንጋት የለበትም::
ቤ/ክርስቲያን ለልጆችና ለታዳጊ ወጣቶች የምትሰጠው ትኩረት
በጣም ሊጨምር ይገባል::ይህ ካልሆነ ግን ከጥቂት ዓመታት በኋላ ተረካቢ ትውልድ ልታጣ ትችላለች::ልጆችና ታዳጊ ወጣቶች ላይ
ብዙ ሊደከምባቸው ይገባል::የልጆች አገልግሎት ለተወሰኑ ሰዎች ተጥሎ ባወጣ ያውጣው ሊባል አይገባም::የቤ/ክርስቲያን ሙሉ ጊዜ
አገልጋዮችና መሪዎች ትኩረት ሊሰጡት ይገባል::ስንት አብያተክርስቲያናት ናቸው ለልጆችና ለታዳጊ ወጣቶች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ
የመደቡት?ይህ ጥያቄ ሲነሳ የበጀት ጉዳይ ሊነሳ ይችል ይሆናል፤ሆኖም ግን ከልብ ካለቀሱ እንዲሉ የገንዘብ ችግር ብቻ ሳይሆን
የእይታም ችግር ነው ያለብን::
አንዱ ችግር በአሁኑ ወቅት የሙሉ ጊዜ አገልጋይና
የቤ/ክርስቲያን መሪ የሆኑ ሰዎች በአብዛኛው ስለ ልጆች አገልግሎት ተገቢ የሆነ ግንዛቤ የሌላቸው መሆኑ ነው::የተለምዶ አሠራር
ከመከተል ውጪ ታስቦበትና ተጨንቆ የልጆችን አገልግሎት ማካሄድ ከእይታቸው ውጪ መሆኑን ማየት አይቸግርም::ይህን ችግር ለመቅረፍ
ለመሪዎችና ለሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ጉዳዩ ያገባናል በሚሉ ወገኖች አግባብነት ያለው ሥልጠና ሊሠጥ ይገባል::ያን ጊዜ ስለ ልጆች
አገልግሎት የመሪዎች ዓይን ይከፈታል::በልጆች ውስጥ ትውልድን ማየት ይችላሉ::ሕጻናትን ሳይሆን ትውልድን አሻግረው ማየት
ይችላሉ::
የልጅነት ጊዜ በሰው ሕይወት ውስጥ ዋና ዋና የሆኑ ነገሮች
የሚቀረጹበት ወቅት በመሆኑ ወሳኝ ነው::አንድ ጥናት እንዳመለከተው 75% የሆኑት የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በልጅነታቸው በሰንበት
ት/ቤት በእግዚአብሔር ቃል ተኮትኩተው ያደጉ ናቸው:: በልጅነት ጊዜ የሚዘራ መልካም ዘር ለኋለኛው የሕይወት ዘመን እጅግ ጠቃሚ
መሠረት እንደሆነ የእግዚአብሔር ቃልም ሆነ የስነ ልቦና አስተምሮ ይነግረናል::"ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው
በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም" (ምሳሌ22:6):: የስነ ልቦና ምሁራን የተናገሩትን ጠቅሶ አንድ ሰው እንዲህ
ብሏል፥"አንድን ልጅ በተገቢ ሁኔታ የመጀመሪያውን 9 ዓመታት ካሳደግከው፥ከ11 እስከ 20 ዓመት ያለውን የዕድሜ ዘመኑን
ትታደጋለህ፤ከ11-20 ያለውን የዕድሜ ዘመኑን በሚገባ ኮትኩተህ ከያዝከው ደግሞ ከ21-90 ዓመት ባለው የሕይወት ዘመኑ መልካም
ሕይወት እንዲመራ ትረዳዋለህ::" (90 ዓመት ለመኖር ከታደለ ማለት ነው)
መልካም ነገሮችን የመዝሪያው ዕድሜ የአዋቂነት የዕድሜ
ክልል አይደለም፤አዋቂዎችን ለመለወጥ እጅግ ይቸግራል(አይቻልም ባይባልም)::ልጆች ግን ምንም ነገር እንዳልተጻፈበት ነጭ ወረቀት
የሆነ አእምሮ ስላላቸው የፈለግነውን ሁሉ በማስተማር በቀላሉ በጎ ተጽዕኖ ልናመጣባቸው እንችላለን (መጥፎ ተጽዕኖ ለማምጣትም
አመቺው ጊዜ የልጅነት ወቅት መሆኑን ሳንዘነጋ)::
ቤ/ክርስቲያን የልጅነት ዕድሜ መልካም ዘር ለመዝራት
ተገቢው ወቅት መሆኑን አውቃ ለአዋቂዎች የምትሰጠውን ያህል ትኩረት ለልጆች በመስጠት ልጆችን በመልካም መሠረት ላይ ልታንጽ
ይገባል::ትኩረት መስጠት ስንል በደፈናው አይደለም::የሚለካ ሊሆን ይገባል::ይህም ማለት ከበጀቷ ስንት ስንተኛው ነው በልጆችና
በልጆች ተዛምዶ ባለው ነገር ላይ የዋለው?የልጆች የመነቃቂያ ጊዜ ወይም ኮንፍራንስ አቅዳለች? የልጆች ሪትሪት ጊዜ
አላት?ለልጆች አገልግሎት የሙሉ ጊዜ አገልጋይ መድባለች?እነደዚህ ዓይነት ፕሮግራሞችን አቅዶ ለማሳካት
ማሰብን፥መነቃነቅን፥ድካምን፥ ብርቱ ጥረትንና የማያቋርጥ ክትትልን ይጠይቃል::የልጆች አገልግሎት እገሌ ይስራው ተብሎ የሚወረወር
ጉዳይ አይደለም::የቤ/ክርስቲያን መሪዎች በአዋቂዎች የተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ እንደምንረባረበው ሁሉ ለልጆችም አገልግሎት እኩል
ትኩረት ልንቸር ይገባል::ከዚህ አቅጣጫ የአመለካከት ለውጥ ልናመጣ ይገባል::ታዋቂው ሳይንቲስት አልበርት አይንስታን እንዲህ
ብሏል፥" አንድን ነገር በተለመደው መንገድ እየሠራህ የተለየ ውጤት የምትጠብቅ ከሆነ አብደሀል ማለት ነው::" በተመሳሳይና
በተለመደው መንገድ የልጆችን አገልግሎት እየመራን ለውጥ እናመጣለን ማለት ዘበት ነው::
በልጆች አገልግሎት የተሳካላቸው አብያተክርስቲያናት ካሉም
ተመክሯቸውን መቅሰም ይገባል::የልምድ ልውውጥ ጊዜ በማዘጋጀት መማማር ይቻላል::በአዲስ አበባ የት/ት ቢሮ አማካኝነት በተቀናጀ
መርሐ ግብር በግል ት/ቤቶች መካከል እየተካሄዱ ያሉ የልምድ ልውውጥ ጊዚያት ለየት/ት ቤቶቹ ያስገኙት ፋይዳ እጅግ ጠቃሚ
መሆኑኑ በዝግጅቶቹ ላይ የተሳተፉ የት/ት ባለሙያዎች ያውቁታል::አብያተክርስቲያናትም የልጆችን አገልግሎት በተመለከተ የልምድ
ልውውጥ መርሐ ግብር ቢያዘጋጁ ጠቀሜታው እጅግ የጎላ ነው::በተጨማሪም ጉዳዩ ያገባናል በሚሉ ወገኖች የምክክር ጊዜ(Panel
Discussion) ቢዘጋጅ ብዙ ትምህርት ሊቀሰምበት እንደሚችል እምነት አለኝ::በልጆች አገልግሎት አቅጣጫ በእኔ እይታ ፈር
ቀዳጅና ስኬታማ ሥራ በኢትዮጵያ እየሠራ የሚገኘው በወንድም ኤፍሬም የሚመራው ሻረን የልጆች አገልግሎት ለብዙዎች
አብያተክርስቲያናት ግንዛቤ በማስጨበጥ ትልቅ ሚና መጫወት እንደሚችል እምነቴ ነው::
በርግጥ የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ ለልጆች የተስተካከለ መንፈሳዊ
እድገት ኃላፊነቱ የቤ/ክርስቲያን ብቻ ነው የሚል እሳቤ የለውም::ወላጆች የበለጠ ኃላፊነት አለባቸው::ሆኖም ግን ቤ/ክርስቲያን
የአገልግሎት ኃላፊነቷን ለመወጣት ስትንቀሳቀስ ለአዋቂዎች የምትሰጠውን ያህል ትኩረት ለልጆችም አገልግሎት ልትነፍግ
አይገባም::ለልጆች የምንሰጠው አገልግሎት ምን ይመስላል?ልንፈትሽ ይገባል::የዛሬው ልጆች የነገ ታዳጊ ወጣቶች ናቸው፤የዛሬ
ታዳጊ ወጣቶች የነገው ወጣቶች ናቸው::የዛሬው ወጣቶች የነገው የቤ/ክርስቲያን መሪዎች ናቸው::በርግጥ ብስለት ያላቸው አንዳንድ
ወጣቶች ዛሬም የቤ/ክርስቲያን መሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ፤የሆኑም አሉ::ጢሞቴዎስ ወጣት የቤ/ክርቲያን መሪ እንደነበረ መጽሐፍ
ቅዱስን ዋቢ አድርገን መጥቀስ እንችላለን::
የልጆችን አገልግሎት ጠቄሜታን በተመለከተ ከwww. Ministry.To-Children.com
ከተሰኘ ድዕረ ገጽ ላይ በመውሰድ ወደ አማርኛ የመለስኩትን ጠቃሚ ነጥቦች ከዚህ በታች በማስነበብ ጹሁፌን እደመድማለሁ::
የልጆች አገልግሎት ጠቀሜታው
ሀ. ለልጆች ያለው ጠቀሜታ
እግዚአብሔር ስለ ልጆች ይገደዋል፤እኛም ስለነሱ ሊገደን
ይገባል::ልጆችን በእግዚአብሔር ቃል እውነት ስናገለግላቸው ብዙ የሚያገኙት ነገር አለ::ስምንቱ ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል::
1. ክርስቶስን እንደ ግል አዳኛቸው አድርገው
ለመቀበል ይረዳቸዋል::
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ
ከማንኛውም የዕድሜ ክልል ይልቅ የልጅነት ወቅት ክርስቶስን ለመቀበል የተከፈተ ልብ የሚገኝበት ወቅት ነው:: በሌላ አነጋገር
ልጆች ከአዋቂዎች ይልቅ ለጌታ ቅርብ ልብ አላቸው::ዕድሜያቸው እየጨመረ ሲሄድ ልባቸው እየጠነከረ ሊሄድ ይችላል::በመሆኑም
በልጅነት ስለ ጌታ ኢየሱስ አዳኝነት መማራቸው ለመዳናቸው መንገድን ይከፍታል::
2. የሕይወት ትርጉም እንዲገባቸው ያደርጋል::
ግኡዙን አለም ማን እንደፈጠረው ማወቃቸው፥የሰውን ውድቀትና
እግዚአብሔር የማዳንን መንገድ ማዘጋጀቱን መገንዘባቸው ለሕይወታቸው ትርጉም ይሰጠዋል::ለምን እንደሚኖሩ ከታናሽነታቸው ጀምሮ
ይገባቸዋል::ለምን እንደሚኖር የገባው ሰው ትርጉም ያለው ሕይወት ይመራል::
3. ዘለቄታዊ ደስታን እንዲያጎለብቱ ይረዳቸዋል::
እግዚአብሔርን በማምለክ የሚገኘውን እውነተኛ ደስታ
እንዲለማመዱ ይረዳቸዋል::በጌታ ደስ መሰኘትን ይማራሉ::እግዚአብሔር የእውነተኛ ደስታ ምንጭ ነውና::
4. አላስፈላጊ ከሆኑ አንዳንድ የኃጢአት አስከፊ
ውጤቶች እንዲጠበቁ ይረዳቸዋል::
በርግጥ የእግዚአብሔር ፀጋ ብቻ ነው ልባችንን መቀየር
የሚችለው::ሆኖም ግን እግዚአብሔርን አለመታዘዝ የሚያስከትለውን አስከፊ ጣጣ በልጅነት ማወቃቸው ልጆችን ጠንቃቃ እንዲሆኑ
ይረዳቸዋል::ኢየሱስ ሊያድናቸው የከፈለውን ትልቅ ዋጋ ሲረዱ፥በጽድቅ መንገድ ለመጓዝ ልባቸውን ያቀናሉ::የእግዚአብሔርን ጽድቅና
ፍቅር ስናሳያቸው በፍቅሩ ልባቸው ሲማረክ፥ጽድቁንና ቅድስናውን ሲያውቁ ደግሞ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸው ልጆች ሆነው
ያድጋሉ::በአክብሮትም ይገዙለታል::
5. የአለማዊነትን በጎ ያልሆነ ተጽዕኖ ለመቋቋም
ይረዳቸዋል::
ሁላችንም በማህበረሰባችን ውስጥ ያለውን ክፉ ተፅዕኖ
እናውቃለን::ይህን በጎ ያልሆነ ተፅዕኖ መቋቋም እንዲችሉ በጎና አዎንታዊ ተፅዕኖ የሚያመጣባቸው አካል ያስፈልጋቸዋል::ያም
አካል የወላጆችና የቤ/ክርስቲያን ጥምር አስተዋፆ ነው::
6. ሌሎችን መውደድን ይማራሉ::
ሁለተኛው ታላቁ ትዕዛዝ "ባልንጀራህን እንደ ራስህ
ውደድ" የሚለው ነው::ይህን ደግሞ በልጆቻችን ላይ ልናሰርጽ የምንችለው ለተቸገሩት ስንጸልይና ስንረዳ ሲያዩ
ነው::ርህራሄ ተሞልተው እንዲያድጉ የሚታይ የፍቅር ሥራ እንደ ወላጅም እንደ ቤ/ክርስቲያን ልናሳያቸው ይገባል::
7. ጥሩ ጓደኞችን የሚያገኙበት ሥፍራ ይሆናል::
ልጆች ጥሩ ጓደኛ ከሚያገኙበት ሥፍራ አንዱ ቤ/ክርስቲያን
ነው::
8. ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚተዋወቁበትና ዝማሬን
የሚማሩበት ሥፍራ ይሆናል::
የቃል ጥቅሶችን እንዲያጠኑ ሲደረግ በአእምሮአቸው
ስለሚሰርጽ በጎ ተጽዕኖ ያመጣባቸዋል::የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክንም እንዲማሩ ይረዳቸዋል::ዝማሬዎችንም በመስማትና
በመዘመር እንዲያድጉ ያደርጋቸዋል::
ቤ/ክርስቲያን በዛሬው ተግባሯና በወደፊቱ ውጥኗ ለልጆችና
ለታዳጊ ወጣቶች አገልግሎት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ወደ አዋቂዎች ያዘመመው አገልግሎቷ ሚዛናዊ ይሁን እላላሁ::አዋቂዎችንም
ችላ እንበል የሚል እንድምታም የለኝም::ሁለቱንም እኩል እናገልግል::ያን ጊዜ ነው አገልግሎታችን ሙሉ የሚሆነው:: ጌታ
ሁላችንንም ይባርክ!
No comments:
Post a Comment