Monday, November 19, 2012



ተሐድሶ 

የነህምያ መጽሃፍን መሰረት ያደረገ ትምህርት

ተሐድሶ ማለት ሁኔታዎች እግዚአብሔር ወዳሰበው ወይም ወዳሰመረው መስመር ሲመጡ ማለት ነው:: በአሁኑ ጊዜ ያለችው ቤተ ክርስቲያን በሐዋሪያት ዘመን ከነበረችው ቤተ ክርስቲያን በእጅጉ የተለየች ሆናለች:: ይህም ከቅድስና፥ ከፍቅርና እግዚአብሔርን ከመፍራት አንጻር ሊታይ ይችላል:: እንደ ቤተ ክርስቲያን የት ነው ያለነው? እንደ ክርስቲያን ተሐድሶ አያስፈልገንም? ቤተ ክርስቲያን ያለነቀፋና ያለምንም ፊት መጨማደድ መሆኗ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው:: ተሐድሶ እንዲመጣ ምን ቅድመ ሁኔታ ሊሟላ ይገባል?  

ተሐድሶ እንዲመጣ ሦስት ቅድመ ሁኔታዎች

•         የነገሮች ወይም ሁኔታዎች መበላሸት ወይም የቀድሞ ሁኔታቸውን ማጣት

•         በሁኔታዎቹ መበላሸት የሚቆጭና የሚያዝን ሰው መኖር (ሸክም ያለው ሰው መኖር)

•         የተበላሸው ሁኔታ እንዲቀየር ርምጃ የሚወስድ ሰው መኖር (ዋጋ የሚከፍል ሰው መገኘት)  

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተሐድሶ ካመጡ ሰዎች አንዱ ነህምያ ነው::  የነህምያን መጽሐፍ ስንቃኝ ከላይ የተጠቀሱት ሶስት ሁኔታዎች ተሟልተው እናገኛለን::  

1-     በመጀመሪያ ደረጃ የኢየሩሳሌም የቀድሞ ሁኔታ ተበላሽቶ ነበር:: ቅጥሮቿ ፈርሰው፥ በሮቿ ተቃጥልው፥ ሕዝቧ ተማርከውና ከምርኮ የተረፉትም በታላቅ ጉስቁልና ውስጥ ነበሩ (ነህምያ 1:3):: በአጠቃላይ የህዝቡ ውጫዊ (Physical) እና መንፈሳዊ (Spiritual) ሁኔታ የተበላሸ ነበር::  

2-    በሁለተኛ ደረጃ ስንመለከት ሁኔታውን ሲያይ የተቆጨ፥ ያዘነና ትልቅ ሸክም የወደቀበት ሰው ነበር:: ያም ሰው ነህምያ ነበር:- "ይህንም ቃል በሰማሁ ጊዜ ተቀምጬ አለቀስሁ፥አያሌ ቀንም አዝን ነበር::በሰማይም አምላክ ፊት እጾምና እጸልይ ነበር" (ነህምያ 1:5-11)::  

3-   በመቀጠልም የተበላሸውን ሁኔታ ለማስተካከል እርምጃ የወሰደን ሰው እናገኛለን:- ነህምያ:: የመጀመሪያው ርምጃ በጌታ ፊት መጾምና መጸለይ ነበር:: ከዚያም እግዚአብሔር ሁኔታዎችን ሲያመቻችለት ለንጉሱ ጥያቄ አቀረበ:: በመቀጠልም የምቾት ቀጠናውን በመተው ወደ ኢየሩሳሌም የሚወስደውን ረጅም ጉዞ ተያያዘው:: ዋጋ ሳይከፈል ተሀድሶ አይመጣም:: የተሃድሶ ሰዎች ቁርጠኞች ናቸው:: ተሐድሶን በተመለከተ ሌላ የምናስተውለው ነገር ለተሀድሶ መነሳት አንድ ሰው በቂ መሆኑን ነው:: ይህ ሰው የነቃ፥ የተነቃቃና የሚያነቃቃ ሲሆን ሁኔታዎች መለወጥ ይጀምራሉ:: ነህምያ የተበላሸ ሁኔታ እንዳለ ሲያይ ይህ ልክ አይደለም ብሎ ነቃ:: በመቀጠልም በጾምና በጸሎትተነቃቃ:: በመጨረሻም ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ሕዝቡን አነቃቃ:: እንዲህ አላቸው:- "እኛ ያለንበትን ጉስቁልና፥ኢየሩሳሌም እንደ ፈረሰች፥ በሮቿም በእሳት እንደ ተቃጠሉ ታያላችሁ:: አሁንም ከእንግዲህ ወዲህ መሳለቂያ እንዳንሆን ኑና የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንሥራ" (ነህ 2:17):: ይህንን ሲሰሙ ሕዝቡ ተነቃቁ:- "እንነሣና እንሥራ" አሉ (ነህ 2:18)::

ተሐድሶና ተግዳሮቶች(Challenges)

ተሐድሶ ለማምጣት የሚንቀሳቀስ ሰው የተለያዩ ተግዳሮቶች ይገጥሙታል:: ነህምያም በእስራኤላውያን መካከል ተሐድሶ ለማምጣት ሲንቀሳቀስ የተለያዩ ተግዳሮቶች ገጥመውታል:: ለእያንዳንዱ ተግዳሮት ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ወደ ተሐድሶ ሊደርስ ችሏል:: ከዚህ በመቀጠል ነህምያ የገጠሙትን ስድስት ተግዳሮቶችና ለነዚህም ተግዳሮቶች የሠጠውን ምላሽ እናያለን::  

1-     ነህምያ ለተሐድሶ ሲንቀሳቀስ የገጠመው የመጀመሪያው ተግዳሮት የተቃዋሚዎች የንቀት ሳቅ ነበር:- "በንቀት ሳቁብን" (ነህ 2:19) ሲል ነህምያ ይገልጸዋል:: አላማውም ተሰፋ ለማስቆረጥ ነበር:: ለዚህ ነህምያ የሠጠው ምላሽ የእምነት ቃል መናገር ነበር:- " የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል:: እኛም ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን" (ነህ 2:20):: ለተሐድሶ ስንነሳ ሰይጣን ተስፋ ሊያስቆርጠን ይሞክራል:: እኛም እንደ ነህምያ የእምነት ቃል በመናገር ወደሚቀጥለው ሥራ መሸጋገር አለብን::  

2-    ይህ ባልተሳካ ጊዜ የነህምያ ጠላቶች በቁጣና በብስጭት በመነሳት በአይሁድ ላይ ማላገጥና መቀለድን ተያያዙ:-"በድንጋይ በሚሠሩት ቅጥራቸው ላይ ቀበሮ ቢመጣበት ያፈርሰዋል" የሚል ፌዝ አፌዙ (ነህ 4:3):: አሁንም አላማቸው ተስፋ በማስቆረጥ እና ልባቸውን በማድከም ከተሐድሶው ሥራ ለመግታት ነበር:: ነህምያ ለዚህ የሠጠው ምላሽ እየጸለየ ሥራውን ማቀላጠፍ ነበር (ነህ 4:5-6):: ከዚህም የተነሣ የቅጥሩ ሥራ በዚህ ሰዓት እስከ እኩሌታው ተጋጠመ (ነህ 4:6):: በተሐድሶ የተግባር ሂደት ውስጥ የሚገጥሙንን የጠላት ፌዝና ልብ አድካሚ ተገዳሮቶችን ለጌታ በጸሎት በመንገር ሥራችንን ማቀላጠፍ ነው ያለብን:: የትኩረት አቅጣችንን ለማግኘት ጠላት ደፋ ቀና ማለቱን አይተውም:: ሁልጊዜ በጸሎት መንፈስ ውስጥ ልንሆን ይገባል::

3-   ቀጣዩ የጠላት ስትራቴጂ እስራኤልን ለመውጋትና ለማሸበር መማማል ነበር (ነህ 4:8):: ይህንንም የጠላት ሤራ ለማክሸፍ እነ ነህምያ ያደረጉት የሚከተለውን ነው:- "ወደ አምላካችንም ጸለይን፥ከእነርሱም የተነሣ በአንጻራቸው ተጠባባቂዎች በሌሊትና በቀን አደረግን::...ከቅጥሩም በስተኋላ በኩል ባለው በታችኛው ስፍራ ሰይፋቸውን፥ጦራቸውንም ቀስታቸውንም አስይዤ ሕዝቡን በየወገናቸው አቆምኋቸው"( ነህ 4:9 13):: ለተሐድሶ የሚነሱ ሰዎች የጠላት ኢላማ መሆናቸው የማይቀር ነው:: በመሆኑም በጌታና በኃይሉ ችሎት በመበርታት ጠላትን በመዋጋት፥ዕቅዱንና አሳቡን ሊያፈርሱ ይገባል:: ምሽግን ለማፍረስ ብርቱ የሆኑ መንፈሳዊ የጦር ዕቃዎች አሉን:: የእግዚአብሔርን ቃል፥ እምነት፥ የኢየሱስን ስም፥ የህብረት ጸሎትና የደሙን ኅይል በመጠቀም የጠላትን ውጊያ ሁሉ ልናፈርስ ይገባል:: የምንዋጋው ከተሸነፈ ጠላት ጋር መሆኑን መዘንጋት የለብንም (ቆላስያስ 2:15፥ ዕብራውያን 2:14151 ጴጥሮ 3:22)::  

4-   ሌላው ነህምያ የገጠመው ተግዳሮት በእስራኤላውያን መሐከል የተነሣው የውስጥ ችግር ነበር:: የነበረባቸው የኢኮኖሚ ችግር የተጀመረውን ተሐድሶ ተፈታትኗል:: እስራኤላውያን የእስራኤላውያንን (የወገኖቻቸውን) የእርሻ መሬቶች በብድር ምክንያት ይዘው ነበር:: ሕዝቡ ተርቦ ነበር:: ይህ የውስጥ ችግር ከሌሎቹ ተግዳሮቶች ይልቅ ነህምያን አስቆጥቶት ነበር:: በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ወደ ተሐድሶ ስንገሰግስና በተሐድሶ ውስጥ ስንሆን የሚገጥመን ትልቁ ተግዳሮት ከውጪ የሚመጣው የጠላት ሠልፍ ወይም ውጊያ ሳይሆን በቅዱሳን መካከል የሚነሳው ጠብና ሹኩቻ ነው:: ነህምያ የገጠመውን ችግር በጥበብ ሊፈታው ችሏል:: እኛም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተሐድሶ ወቅት የሚገጥመንን ችግር በጠብ ሳይሆን በጥበብ ልንፈታው ይገባል:: በታሪክ ውስጥ ስናይ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተነሡ ተሐድሶዎች ሊገቱ የቻሉት በቅዱሳን መካከል በተነሱ አለመግባባቶች፥ ፀቦች፥ ሹኩቻዎችና ራስ ተኮር(Self Centered Life Style) አካሄዶች እንጂ ከውጪ በሆነ ውጊያ አለመሆኑን እንገነዘባለን:: እግዚአብሔርን ያላማከለ ሕይወትና የራስን ክብር መፈላላግ የመስቀሉ ጠላቶች በመሆን የጌታን ሥራ ያበላሻሉ:: ለዚህ መፍትሄው ራስን መካድና ለጌታ ደስታ መኖር ነው::  

5-   በተሐድሶ ግስገሳ ውስጥ ሌላው ነህምያን የገጠመው ተግዳሮት ሽንገላ ነው:: ጠላቶቹ ከዚህ በፊት የሞከሩት አፍራሽ ስልት ሁሉ እንዳልተሳካና የማደሱ ሥራ ሳይገታ መቀጠሉን ሲያዩ ሌላ ዘዴ ይዘው መጡ:-ሽንገላ:: ለርሱ የተቆረቆሩ በመምሰል ነህምያን ለምክክር ስብሰባ አምስት ጊዜ ጠሩት:- "እንግዲህ መጥተህ በአንድነት እንማከር"የሚል ጥሪ ነበር (ነህ 6:2-9):: ለዚህም ሽንገላ ነህምያ የሠጠው ምላሽ "ትልቅ ሥራ እሠራለሁ፥ እወርድም ዘንድ አይቻለኝም" የሚል ነበር:: ጠላት ሁልጊዜ የሚፈልገው የጀመርነውን የተሐድሶ ሥራ አቋርጠን ከከፍታችን እንድንወርድ ነው:: በተሐድሶ ሥራ ውስጥ ያለ ሰው ለጠላት ሽንገላ አግባባዊ መልስ ሊሠጥ ይገባል እንጂ የትኩረት አቅጣጫውን ሊስት አይገባም::  

6-   የመጨረሻው የጠላት ሙከራ ሐሰተኛ ነብይ በመላክ ነህምያን ለማሳሳት መሞከር ነበር:: ነህምያ ማድረግ የማይገባውን ነገር እንዲያደርግና በደል እንዲፈጽም ለማሳሳት ነበር(ነህ 6:10-14):: ሆኖም ነህምያ የጠላቶቹን ሤራ በማስተዋል ከስህተት ሊጠበቅ ችሏል:: የዲያቢሎስን ሽንገላ እንድንቃወም የእግዚአብሔር ቃል ያሳስበናል (ኤፌሶን 6:11):: ዓለምን ያሳተው የቀደመው እባብና ዘንዶ (ሰይጣን ወይም ዲያቢሎስ) ዋናው ሥራ በመሸንገል ማሳት ነው:: በእግዚአብሔር ቃልና በጥበብ በመሞላት ሤራውን ልናስተውል ይገባል:: "በሰይጣን እንዳንታለል የእርሱን አሳብ አንስተውምና" ይላል ቃሉ (2 ቆሮ.2:11)::  

እነዚህን ሁሉ ተግዳሮቶች በድል ከተወጣ በኋላ ነህምያ ለተሐድሶ መምጣት ምክንያት መሆን ችሏል:: እልህ አስጨራሽ የነበረውን ውጣ ውረድና ፈተና ካለፉ በኋላ እነ ነህምያ የሚከተለውን ውጤት ለማየት በቅተዋል:-

በነህምያ መጽሃፍ የተጠቀሱ የተሐድሶ ውጤቶች

1. ቅጥሩን የማደስ ሥራ 52 ቀናት ማጠናቀቅ ችለዋል( ነህ 6:15)  
2. ጠላቶቻቸውን ሁሉ ማሳፈር ችለዋል (ነህ 6:16)  
3. ከዚህም የተነሳ መንፈሳዊ ተሐድሶ ሊመጣ ችሏል:- እስራኤላዊያን ሁሉ በእግዚአብኤር ፊት ኃጢአታቸውንና የአባቶቻቸውን ኃጢአት ተናዘዋል (ነህ 9:3)  
4. ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ቃል ሊሰሙ ችለዋል (ነህ 9:3)  
5. ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ሰገዱ (ነህምያ 9:3)  
6. በሕዝቡ መሐከል እጅግ ታላቅ ደስታ ሆነ (ነህ 8:17)  
7. ሕዝቡም ተቀደሱ (ነህ 9:2)  

መደምደሚያ

የተሐድሶ ግብ ቅዱሳን ኃጢአታቸውን በመናዘዝና በመተው በመንፈስና በእውነት እግዚአብሔርን ወደ ማምለክ ሲመጡ ነው:: እግዚአብሔርን በመፍራት መቀደስ ሲችሉ እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል በክብሩ ይመላለሳል:: እግዚአብሔርም ይከብራል:: የመኖራችን ግብ እግዚአብሔርን ማስከበር ከሆነ በተሐድሶ ሕይወት ውስጥ መሆናችንን ልንገነዘብ ይገባል:: በተቃራኒው ሁሉጊዜ ስለራሳችን ጥቅም፥ክብር እና ዝና የምናስብና በሥጋዊ ምኞት የተዋጥን ከሆነ ተሐድሶ ያስፈልገናል:: ለተፈጠርንለት አላማ እየኖርን አይደለም:: ጌታ ሆይ በተሀድሶ ጎብኘን ብለን ልንጸልይ ይገባል:: እግዚአብሔር ያየልንን ሕይወት ኖረን እንድናልፍ ጌታ ይርዳን:: ጥሪያችን እንደ ንስር እንድንኖር እንጂ እንደ ዶሮ ምድር ምድር እያየን ምድራዊ ሆነን እንድንቀር አይደለም:: ተሐድሶ ቤተክርስቲያን ጌታን የምትወድ፥ያለ ነቀፋና ያለ ምንም ፊት መጨማደድ የሆነች እንድትሆን ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል::
 

በወንድም ተድላ ሲማ


No comments:

Post a Comment