Wednesday, November 7, 2012


ወደ እግዚአብሔር መቅረብ


"... ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል::" ያዕ 4:8
ወደ እግዚአብሔር እንዴት እንቅረብ?

1. በምሥጋናና በውዳሴ መዝ. (34): 1፥ ዕብ.13:15
ሁልጊዜ ወደ እግዚአብሄር ፊት በምሥጋና ልንቀርብ ይገባል:: 
ምሥጋና የምናቀርበው ከጌታ ለተቀበልናቸው ነገሮች ሁሉ ነው:: ስለጤንነታችን፥ ስለምንበላው ምግብ፥ ስለምንተነፍሰው አየር፥ ስለ ሰጠን ሥራ፥ ስለ ቤተሰባችን፥ ስለ መዳናችንና ስለ ሌሎችም ስለተቀበልናቸው ነገሮች ጌታን ልናመሰግን ይገባል:: በግል የአምልኮ ህይወታችን ምሥጋናን ልንለማመድ ይገባል::
ውዳሴ ማለት የእግዚአብሄርን ታላቅነት መናገር ማለት ነው::እግዚአብሄርን ታላቅ ነህ ኅያል ነህ ሁሉን ቻይ ነህ የሚመስልህ የለም ቅዱስ ነህየነገሥታት ንጉሥ ነህ የአማልክት አምላክ ነህየጌቶች ጌታ ነህ አዋቂ ነህብርቱ ነህየሠራዊት ጌታ ነህ የኅያላን ሁሉ ኅያል ነህ ሠማይን የሠራህ የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ፀሀይንና ጨረቃን የፈጠርክ ከዋክብትን በስማቸው የምትጠራ የኤርትራን ባህር የከፈልክ ህዝብህን ያሻገርክ አልፋና ኦሜጋ ነህ ዘላለማዊ ነህ ማስተዋልህ አይመረመርም ጠቢብ ነህ ስንለውና ታላላቅ ሥራዎቹን ስንናገር እያወደስነው ነው:: ይህንን ሁልጊዜ ልንለማመድ ይገባል:: የተፈጠርነው ጌታን ለማምለክ ነው:: ለመብላትና ለመጠጣት አልተፈጠርንም:: የምንበላውና የምንጠጣው ለመኖር ነው:: የምንኖረው ግን ጌታን ለማምለክ ነው:: እግዚአብሄርን ማመሥገንና ማወደስ አንዱ (ብቸኛው ባይሆንም) የአምልኮአችን መገለጫ ነው::

2. ቃሉን ማንበብ  መስማት  ማጥናት  ማሰላሰልና በቃል ማስታወስ
የእግዚአብሄር ቃል እምነትን (እርግጠኛ ተስፋ) በውስጣችን ይፈጥራል አእምሮን ያድሳል የአስተሳስብ ቅድስና ያመጣል:: ስንጸልይ ከጌታ ኅይል እናገኛለን:: ቃሉን ስናነብ ግን የአስተሳሰብ ለውጥ እናመጣለን:: እንደ እግዚአብሄር ማሰብ እንጀምራለን:: እግዚአብሄር ቃል የእግዚአብሄርን አሳብና ፍላጎት ይናገራል:: በየዕለቱ 4 ምዕራፍ በማንበብ መጽሐፍ ቅዱሳችንን በየዓመቱ አንዴ መጨረስ እንችላለን:: ቢሊ ገርሃም 150 ጊዜ በላይ መጽሐፍ ቅዱስን አንብበዋል:: በመሆኑም እግዚአብሔር የተጠቀመባቸው የወንጌል አገልጋይ ለመሆን በቅተዋል:: ጆርጅ ሙለር የተባሉ የእግዚአብሔር ሰው ደግሞ 300 ጊዜ በላይ መጽሐፍ ቅዱስን አንብበዋል:: በመሆኑም የእምነት ሐዋርያ ለመባል በቅተዋል::  በዘመናቸው ወደ 2000 የሚጠጉ ወላጅ ዐልባ ህፃናትን በእምነት በተገኘ በጀት አሳድገው ለወግ ለማዕረግ አብቅተዋል::

3. በጸሎት ወደ ፊቱ መቅረብ
በየዕለቱ በጸሎት ወደ ጌታ መቅረብ አለብን:: ጌታ ኢየሱስ ወደ አባቱ ፊት መቅረብ እጅግ ደስ የሚያሰኘው ነገር ነበር:: እኛም ወደ አፍቃሪአችን ጌታ ፊት መቅረብ ልንናፍቅ ይገባል:: ለልመና ብቻ ልንቀርብ አይገባም:: ፍቅራችንን ለመግለጽ ወደ ፊቱ መቅረብ አለብን:: ጌታ ሆይ እወድሃለሁ ልንለው ይገባል:: በጸሎት ወደ ፊቱ ስንቀርብ ጌታ መንፈሱንና ኅይሉን ይሞላናል:: ክብሩን ያሳየናል::ክብሩን ስናይ እንጠግባለን:: በየዕለቱ ቢያንስ ለአንድ ሰዓት የጸሎት ጊዜ ቢኖረን መልካም ነው:: ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ ብሏል ጌታ::

4. እግዚአብሔርን ማሰብና ማሰላሰል
ሁልጊዜ እግዚአብሔርን በፊቴ አየዋለሁ በቀኜ ነውና አልታወክም:: ስለዚህ ልቤን ደስ አለው ምላሴም ሐሴት አደረገች:: መዝ. (16): 8 ጌታንና ምህረቱን ቸርነቱንና ቅነቱን ማሰብ ወደ እግዚአብሄር እንድንጠጋ ያደርገናል::

5. ከቅዱሳን ጋር ህብረት ማድረግ መዝ. (133): 1-3
ቅዱሳን የጌታ አካል ስለሆንን በጌታ ህብረት ስናደርግ የጌታን ጸጋ እንከፋፈላለን:: ይህም ወደ እግዚአብሄር እንድንጠጋ ያደርገናል:: እግዚአብሄር በቤተ ክርስቲያን (በቅዱሳን መሰባሰብ በኩል) በኩል ነው ፀጋውን የሚለቀው:: ከቅዱሳን ጋር ጌታን ማምለክ መጸለይ ማገልገል ከጌታ ጋር የጠበቀ ህብረት እንዲኖረን ይረዳል:: ጌታ አብዝቶ ይባርከን!!

በወ/ ተድላ ሲማ 

No comments:

Post a Comment