ተኃድሶ
ተኃድሶ ማለት ሁኔታዎች እግዚአብሔር ወዳሰበው ወይም ወዳሰመረው መስመር ሲመጡ ማለት ነው::በአሁኑ ጊዜ
ያለችው ቤተ ክርስቲያን በአዲስ ኪዳን ጊዜ ከነበረችው ቤተ ክርስቲያን በእጅጉ የተለየች ሆናለች::ይህም ከቅድስና፥ከፍቅርና
እግዚአብሔርን ከመፍራት አንጻር ሊታይ ይችላል:: እንደ ቤተ ክርስቲያን የት ነው ያለነው? እንደ
ክርስቲያን ተሐድሶ አያስፈልገንም? ቤተ ክርስቲያን ያለነቀፋና ያለምንም ፊት መጨማደድ መሆኗ የእግዚአብሔር
ፈቃድ ነው::ተሐድሶ እንዲመጣ ምን ቅድመ ሁኔታ ሊሟላ ይገባል?
ተኃድሶ እንዲመጣ ሦስት ቅድመ ሁኔታዎች
1. የነገሮች ወይም ሁኔታዎች መበላሸት ወይም የቀድሞ ሁኔታቸውን ማጣት
2. በሁኔታዎቹ መበላሸት የሚቆጭና የሚያዝን ሰው መኖር (ሸክም ያለው ሰው መኖር)
3. የተበላሸው ሁኔታ እንዲቀየር ርምጃ የሚወስድ ሰው መኖር (ዋጋ የሚከፍል ሰው መገኘት)
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተሀድሶ ካመጡ ሰዎች አንዱ ነህምያ ነው::የነህምያን መጽሐፍ ስንቃኝ ከላይ የተጠቀሱት ሶስት ሁኔታዎች ተሟልተው እናገኛለን::
·
በመጀመሪያ ደረጃ የኢየሩሳሌም የቀድሞ ሁኔታ ተበላሽቶ ነበር::ቅጥሮቿ ፈርሰው፥በሮቿ ተቃጥልው፥ሕዝቧ ተማርከውና
ከምርኮ የተረፉትም
በታላቅ ጉስቁልና
ውስጥ ነበሩ (ነህምያ 1:3)::በአጠቃላይ የህዝቡ ውጫዊ (Physical ) እና መንፈሳዊ (Spiritual) ሁኔታ የተበላሸ ነበር::
·
በሁለተኛ ደረጃ ስንመለከት ሁኔታውን ሲያይ የተቆጨ፥ያዘነና ትልቅ ሸክም የወደቀበት ሰው ነበር::ያም ሰው ነህምያ ነበር:-" ይህንም ቃል በሰማሁ ጊዜ ተቀምጬ አለቀስሁ፥አያሌ ቀንም አዝን ነበር::በሰማይም አምላክ ፊት እጾምና እጸልይ ነበር" (ነህምያ 1:5-11)::
·
በመቀጠልም የተበላሸውን ሁኔታ ለማስተካከል እርምጃ የወሰደን ሰው እናገኛለን:-ነህምያ ::የመጀመሪያው ርምጃ በጌታ ፊት መጾምና መጸለይ ነበር::ከዚያም እግዚአብሔር ሁኔታዎችን ሲያመቻችለት ለንጉሱ ጥያቄ አቀረበ::በመቀጠልም የምቾት ቀጠናውን በመተው ወደ ኢየሩሳሌም የሚወስደውን ረጅም ጉዞ ተያያዘው::ተሀድሶ ዋጋ ሳይከፈል አይመጣም:: የተሃድሶ ሰዎች ቁርጠኞች ናቸው::ተሐድሶን በተመለከተ ሌላ የምናስተውለው ነገር ለተሀድሶ መነሳት አንድ ሰው በቂ መሆኑን ነው::ይህ ሰው የነቃ፥የተነቃቃና የሚያነቃቃ ሲሆን ሁኔታዎች መለወጥ ይጀምራሉ::ነህምያ የተበላሸ ሁኔታ እንዳለ ሲያይ ይህ ልክ አይደለም ብሎ ነቃ::በመቀጠልም
በጾምና በጸሎትተነቃቃ:: በመጨረሻም
ወደ ኢየሩሳሌም
በመሄድ ሕዝቡን አነቃቃ::እንዲህ አላቸው:-"እኛ ያለንበትን ጉስቁልና፥ኢየሩሳሌም እንደ ፈረሰች፥በሮቿም በእሳት እንደ ተቃጠሉ ታያላችሁ::አሁንም ከእንግዲህ ወዲህ መሳለቂያ እንዳንሆን ኑና የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንሥራ" (ነህ 2:17)::ይህንን ሲሰሙ ሕዝቡ ተነቃቁ:- "እንነሣና እንሥራ" አሉ (ነህ 2:18)::
ተሐድሶና ተግዳሮቶች(Challenges)
ተሐድሶ ለማምጣት የሚንቀሳቀስ ሰው የተለያዩ ተግዳሮቶች ይገጥሙታል::ነህምያም በእስራኤላውያን መካከል ተሐድሶ ለማምጣት ሲንቀሳቀስ የተለያዩ ተግዳሮቶች ገጥመውታል::ለእያንዳንዱ ተግዳሮት ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ወደ ተሐድሶ ሊደርስ ችሏል::ከዚህ በመቀጠል ነህምያ የገጠሙትን ስድስት ተግዳሮቶችና ለነዚህም ተግዳሮቶች የሠጠውን ምላሽ እናያለን::
1.
ለተሐድሶ ሲንቀሳቀስ ነህምያ የገጠመው የመጀመሪያው ተግዳሮት የተቃዋሚዎች የንቀት ሳቅ ነበር:-"በንቀት ሳቁብን " ሲል ነህምያ ይገልጸዋል::አላማውም ተሰፋ ለማስቆረጥ ነበር::ለዚህ ነህምያ የሠጠው ምላሽ የእምነት ቃል መናገር ነበር:-" የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል::እኛም ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን" (ነህ 2:20)::ለተሐድሶ ስንነሳ ሰይጣን ተስፋ ሊያስቆርጠን ይሞክራል::እኛም እንደ ነህምያ የእምነት ቃል በመናገር ወደሚቀጥለው ሥራ መሸጋገር አለብን::
2.
ይህ ባልተሳካ ጊዜ የነህምያ ጠላቶች በቁጣና በብስጭት በመነሳት በአይሁድ ላይ ማላገጥና መቀለድን ተያያዙ:-"በድንጋይ በሚሠሩት ቅጥራቸው ላይ ቀበሮ ቢመጣበት ያፈርሰዋል" የሚል ፌዝ አፌዙ (ነህ 4:3)::አሁንም አላማቸው ተስፋ በማስቆረጥ እና ልባቸውን በማድከም ከተሐድሶው ሥራ ለመግታት ነበር::ነህምያ ለዚህ የሠጠው ምላሽ እየጸለየ ሥራውን ማቀላጠፍ ነበር (ነህ 4:5-6)::ከዚህም የተነሣ የቅጥሩ ሥራ በዚህ ሰዓት እስከ እኩሌታው ተጋጠመ(ነህ 4:6):: በተሐድሶ የተግባር ሂደት ውስጥ የሚገጥሙንን የጠላት ፌዝና ልብ አድካሚ ተገዳሮቶችን ለጌታ በጸሎት በመንግር ሥራችንን ማቀላጠፍ ነው ያለብን::የትኩረት አቅጣችንን ለማግኘት ጠላት ደፋ ቀና ማለቱን አይተውም::ሁልጊዜ በጸሎት መንፈስ ውስጥ ልንሆን ይገባል::
3.
ቀጣዩ የጠላት ስትራቴጂ እስራኤልን ለመውጋትና ለማሸበር መማማል ነበር (ነህ 4:8)ይህንንም የጠላት ሤራ ለማክሸፍ እነ ነህምያ ያደረጉት የሚከተለውን ነው:-"ወደ አምላካችንም ጸለይን፥ከእነርሱም
የተነሣ በአንጻራቸው
ተጠባባቂዎች በሌሊትና
በቀን አደረግን::...ከቅጥሩም በስተኋላ በኩል ባለው በታችኛው ስፍራ ሰይፋቸውን፥ጦራቸውንም ቀስታቸውንም
አስይዤ ሕዝቡን በየወገናቸው አቆምኋቸው"( ነህ 4:9 ና 13)::ለተሐድሶ የሚነሱ ሰዎች የጠላት ኢላማ መሆናቸው የማይቀር ነው::በመሆኑም በጌታና በኃይሉ ችሎት በመበርታት ጠላትን በመዋጋት፥ዕቅዱንና አሳቡን ሊያፈርሱ ይገባል::ምሽግን ለማፍረስ ብርቱ የሆኑ መንፈሳዊ የጦር ዕቃዎች አሉን::የእግዚአብሔርን ቃል፥እምነት፥የኢየሱስን ስም፥የህብረት ጸሎትና የደሙን ኅይል በመጠቀም የጠላትን ውጊያ ሁሉ ልናፈርስ ይገባል:: የምንዋጋው ከተሸነፈ ጠላት ጋር መሆኑን መዘንጋት የለብንም (ቆላስያስ 2:15፥ዕብራውያን 2:14ና15፥1ኛ ጴጥሮ 3:22)::
4.
ሌላው ነህምያ የገጠመው ተግዳሮት በእስራኤላውያን መሐከል የተነሣው የውስጥ ችግር ነበር::የነበረባቸው የኢኮኖሚ ችግር የተጀመረውን ተሐድሶ ተፈታትኗል::እስራኤላውያን የእስራኤላውያንን(የወገኖቻቸውን)
የእርሻ መሬቶች በብድር ምክንያት ይዘው ነበር::ሕዝቡ ተርቦ ነበር::ይህ የውስጥ ችግር ከሌሎቹ ተግዳሮቶች ይልቅ ነህምያን አስቆጥቶት ነበር::በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ወደ ተሐድሶ ስንገሰግስና በተሐድሶ ውስጥ ስንሆን የሚገጥመን ትልቁ ተግዳሮት ከውጪ የሚመጣው የጠላት ሠልፍ ወይም ውጊያ ሳይሆን በቅዱሳን መካከል የሚነሳው ጠብና ሹኩቻ ነው:: ነህምያ የገጠመውን ችግር በጥበብ ሊፈታው ችሏል::እኛም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተሐድሶ ወቅት የሚገጥመንን ችግር በጠብ ሳይሆን በጥበብ ልንፈታው ይገባል::በታሪክ ውስጥ ስናይ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተነሡ ተሐድሶዎች ሊገቱ የቻሉት በቅዱሳን መካከል በተነሱ አለመግባባቶች፥ፀቦች፥ሹኩቻዎችና ራስ ተኮር(Self Centered Life Style) አካሄዶች
እንጂ ከውጪ በሆነ ውጊያ አለመሆኑን እንገነዘባለን::እግዚአብሔርን ያላማከለ
ሕይወትና የራስን ክብር መፈላላግ የመስቀሉ ጠላቶች በመሆን የጌታን ሥራ ያበላሻሉ::ለዚህ መፍትሄው ራስን መካድና ለጌታ ደስታ መኖር ነው::
5.
በተሐድሶ ግስገሳ ውስጥ ሌላው ነህምያን የገጠመው ተግዳሮት ሽንገላ ነው::ጠላቶቹ ከዚህ በፊት የሞከሩት አፍራሽ ስልት ሁሉ እንዳልተሳካና የማደሱ ሥራ ሳይገታ መቀጠሉን ሲያዩ ሌላ ዘዴ ይዘው መጡ:-ሽንገላ::ለርሱ የተቆረቆሩ በመምሰል ነህምያን ለምክክር ስብሰባ አምስት ጊዜ ጠሩት:-"እንግዲህ መጥተህ በአንድነት እንማከር"የሚል ጥሪ ነበር (ነህ 6:2-9)::ለዚህም ሽንገላ ነህምያ የሠጠው ምላሽ "ትልቅ ሥራ እሠራለሁ፥እወርድም ዘንድ አይቻለኝም" የሚል ነበር::ጠላት ሁልጊዜ የሚፈልገው የጀመርነውን የተሐድሶ ሥራ አቋርጠን ከከፍታችን እንድንወርድ ነው::በተሐድሶ ሥራ ውስጥ ያለ ሰው ለጠላት ሽንገላ አግባባዊ መልስ ሊሠጥ ይገባል እንጂ የትኩረት አቅጣጫውን ሊስት አይገባም::
6.
የመጨረሻው የጠላት ሙከራ ሐሰተኛ ነብይ በመላክ ነህምያን ለማሳሳት መሞከር ነበር::ነህምያ ማድረግ የማይገባውን ነገር እንዲያደርግና በደል እንዲፈጽም ለማሳሳት ነበር(ነህ 6:10-14)::ሆኖም ነህምያ የጠላቶቹን ሤራ በማስተዋል ከስህተት ሊጠበቅ ችሏል::የዲያቢሎስን ሽንገላ እንድንቃወም የእግዚአብሔር ቃል ያሳስበናል (ኤፌሶን 6:11)::ዓለምን ያሳተው የቀደመው እባብና ዘንዶ (ሰይጣን ወይም ዲያቢሎስ) ዋናው ሥራ በመሸንገል ማሳት ነው::በእግዚአብሔር ቃልና በጥበብ በመሞላት ሤራውን ልናስተውል ይገባል::"በሰይጣን እንዳንታለል የእርሱን አሳብ አንስተውምና" ይላል ቃሉ (2ኛ ቆሮ.2:11)::
እነዚህን ሁሉ ተግዳሮቶች በድል ከተወጣ በኋላ ነህምያ ለተሐድሶ መምጣት ምክንያት መሆን ችሏል::እልህ አስጨራሽ የነበረውን ውጣ ውረድና ፈተና ካለፉ በኋላ እነ ነህምያ የሚከተለውን ውጤት ለማየት በቅተዋል:-
በነህምያ መጽሃፍ የተጠቀሱ የተሃድሶ ውጤቶች
1. ቅጥሩን የማደስ ሥራ በ 52 ቀናት ማጠናቀቅ ችለዋል ( ነህ 6:15)
2. ጠላቶቻቸውን ሁሉ ማሳፈር ችለዋል (ነህ 6:16)
3.ከዚህም የተነሳ መንፈሳዊ ተሐድሶ ሊመጣ ችሏል:-እስራኤላዊያን ሁሉ በእግዚአብኤር ፊት ኃጢአታቸውንና የአባቶቻቸውን ኃጢአት ተናዘዋል (ነህ 9:3)
4. ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ቃል ሊሰሙ ችለዋል (ነህ 9:3)
5.ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ሰገዱ (ነህምያ 9:3)
6.በሕዝቡ መሐከል እጅግ ታላቅ ደስታ ሆነ (ነህ 8:17)
7. ሕዝቡም ተቀደሱ (ነህ 9:2)
የተሐድሶ ግብ ቅዱሳን ኃጢአታቸውን በመናዘዝና በመተው በመንፈስና በእውነት እግዚአብሔርን ወደ ማምለክ ሲመጡ ነው:: እግዚአብሔርን በመፍራት
መቀደስ ሲችሉ እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል በክብሩ ይመላለሳል::እግዚአብሔርም ይከብራል::የመኖራችን ግብ እግዚአብሔርን ማስከበር ከሆነ በተሐድሶ ሕይወት ውስጥ መሆናችንን ልንገነዘብ ይገባል::በተቃራኒው ሁሉጊዜ ስለራሳችን ጥቅም፥ክብር እና ዝና የምናስብና በሥጋዊ ምኞት የተዋጥን
ከሆነ ተሐድሶ ያስፈልገናል::ለተፈጠርንለት አላማ እየኖርን አይደለም:ሆ ጌታ ሆይ በተሀድሶ ጎብኘን ብለን ልንጸልይ ይገባል::እግዚአብሔር ያየልንን ሕይወት ኖረን እንድናልፍ ጌታ ይርዳን::ጥሪያችን እንደ ንስር እንድንኖር እንጂ እንደ ዶሮ ምድር ምድር እያየን ምድራዊ ሆነን እንድንቀር አይደለም::ተሐድሶ ቤተክርስቲያን ጌታን የምትወድ፥ያለ ነቀፋና ያለ ምንም ፊት መጨማደድ የሆነች እንድትሆን ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል::
No comments:
Post a Comment